እንኳን ለ2016 ዓ/ም የጌታችንና የመድሃንታችን የእየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረዶ በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን አወጀላቸው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ በታላቅ ኃይልና ሥልጣንም ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ “ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ሆነ” በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲሁም ምዕመናንና ምዕመናት ሰላምታ ከመለዋወጥ አስቀድሞ ይህን ቃል በመናገር የትንሣኤውን አዋጅ ማወጅና መመስከር ይገባቸዋል፡፡
በዘመኑ የነበሩት የካሕናት አለቆች፣ ጸሃፍትና ፈሪሳዊያን ግን በድርጊታቸው ሳይጸጸቱና ሳያፍሩ የክርስቶስን ድል አድራጊነት ከመቀበልና ንሰሃ ከመግባት ይልቅ ትንሳዔውን ለመደብቅና ለመካድ በሀሰት ወሬዎች መጠቀምን መረጡ (ማቴ 28:11)።