እንኩዋን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላም አደረሳችሁ!
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ 12ቱ ደቀ መዛሙርት፣ 72ቱ አርድእትና 36ቱ ቅዱሳት አንስት በኢሩሳሌም ከተማ በአንድነት ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ በሚያርግበት ጊዜም “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤” ሉቃ 24፥49 ሲል ለሐዋርያቱ በገባላቸው ቃል መሠረት ባረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡
በሐዋርያት ሥራ እንደ ተጻፈው በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማለዳ ኹሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሳሉ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጣና የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በኹሉም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁላቸውም መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ሁሉ መናገር ጀመሩ ሐዋ 2፥1-4። ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡
“ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ ለኾነው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስሙ ሲኾን፣ ትርጕሙም በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ናዛዚ (የሚናዝዝ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) ማለት ነው፡፡ በዓለ ጰራቅሊጦስ በሌላ ቃል በዓለ ጰንጠቆስጤ በመባልም ይታወቃል፡፡ ይኸውም በግሪክ ቋንቋ በዓለ ሃምሳ፣ የፋሲካ ሃምሳኛ ዕለት፣ በዓለ ሠዊት (የእሸት፣ የመከር በዓል) ማለት ነው። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ 906 እና 907)