በደብራችን ማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም የተዘጋጀ ታላቅ ኦርቶድክሳዊ ተዋህዶ የወጣቶች ጉባኤ!

ወጣቱንና ዘመኑን የዋጀ ታላቅ ኦርቶድክሳዊ ተዋህዶ የወጣቶች ጉባኤ መምህር ዲያቆን ጎርጎርዮስ ደጀኔን ከሰሜን አሜሪካ ዴንቨር ኮሎራዶ እንዲሁም መምህር ነቅአጥበብ ከፍያልው ከኢትዮጵያ ተጋብዘው በተገኙበት በደብራችን የሚያዘጋጀው ታላቅ የሶስት ቀን የወጣቶች ጉባኤ ከዓርብ ግንቦት 16 እስከ ዕሁድ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ/ም (f.o.m. 24. t.o.m. 26. mai 2024) ድረስ ይካሄዳል።

መርሃግብሩ ለመጀመርያ ጊዜ በወጣት ኦርቶዶክሳውያን ችግርና መፍትሔ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የመንፈሳዊ ስልጠናው እና የዕምነት መርሃግብሩን በመላው ኖርዌይ ያሉ ወጣት የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይሳተፉበታል።

በጉባኤው ላይ ወጣቶች ሊብራራቸው የሚፈልጉትን መንፈሳዊ ጥያቄዎች በማንሳት ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙና መንፈሳዊ ዕውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ታስቦ የተዘጋጀ ስለሆነ በኦርቶድክሳዊ ተዋህዶ ዕምነት ዙሪያ ወጣቶች ግለጽ ያልሆነላቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ነቁ ተሳትፎ እንድያደርጉ የደብሩ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ጥሪውን ያቀርባል።

በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ የምትፈልጉ ወጣቶችና ለተጨማሪ መረጃ የደብሩን የሰንበት ት/ቤት ማነጋገር ይቻላል።

Fredag/አርብ
18:00 – 18:30 እንግዶች ቅበላ እና ትውውቅ
18:30 – 19:00 ጉባኤው በአበው ፀሎት ይጀምራል
19:00 – 19:15 መዝሙር
19:15 – 20:00 ትምሕርት በተጋባዥ መምሕር ዲያቆን ጎርጎርዬስ ደጀኔ
20:15 – 20:20 መዝሙር
20:20 – 20:30 ጉባኤው በአበው ፀሎት ይዘጋል
20:30 የእራት መስተንግዶ

Lørdag/ቅዳሜ
07:30 – 08:30 ፀሎት አስተባባሪ
08:30 – 11:30 የቁርስ መስተንግዶ እና ትውውቅ
11:30 – 12:00 ጉባኤው በአበው ፀሎት ይጀምራል
12:00 – 12:15 መዝሙር
12:15 – 13:00 ትምሕርት በተጋባዥ መምሕር ዲያቆን ጎርጎርዬስ ደጀኔ ዲያቆን ጎርጎርዬስ ደጀኔ
13:00 – 13:30 እረፍት
13:30 – 14:30 ጥያቄ እና መልስ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ከፍያለው
14:30 – 15:00 መዝሙር
15:00 – 17:00 ምሳ
17:00 – 18: 00 ጥያቄ እና መልስ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ከፍያለው እና ዲያቆን ጎርጎርዬስ ደጀኔ
18:00 – 18:30 መዝሙር
18:30 – 20:30 የእራት መስተንግዶ እና ትውውቅ

Søndag/እሁድ
06:30 – 11:00 ቅዳሴ
11:00 – 12:00 ትምህርት እና መዝሙር መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ከፍያለው እና ዲያቆን ጎርጎርዬስ ደጀኔ
12:00 – 13:00 ምሳ እና እንግዶች ሽኝት

እንኳን ለዳግም ትንሳዔ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የትንሳዔ ዕለት ለአስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከላቸው ተገኝቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ብሎ ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ቶማስ ከሔደበት አገልግሎት ሲመለስ የጌታችንን መነሣትና እንደተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ዐየን ብላችሁ ልትመሰክሩ፣ ልታስተምሩ፣ እኔ ግን «ሰምቼአለሁ» ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ ጌታችን መድኀኔዓለም ክርስቶስ ልክ እንደመጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ ለሁለትኛ ጊዜ ተግልጾላቸዋል። በዚሁም መሰረት ለሁለተኛ ጊዜ ቶማስ ባለበት በግልጥ የታየበት ዕለት ሰለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ዳግም ትንሣኤ በማለት ይህንን ዕለት ታከብረዋለች፡፡

“ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው”። ከዚያም በኋላ ቶማስን ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው። ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም። ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው። (የዮሐንስ ወንጌል – ምዕራፍ 20፥26-29)።

ስለዚህ ይህ ሰንበት የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ «ዳግም ትንሣኤ» ተብሎ ከትንሳዔ ባልተናነሰ መልኩ ይከበራል፡፡

የዕመቤታችን ቅድስትድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በድምቀት ተከብሮ ዋለ

የዕመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ/ም (torsdag 09. mai 2024) በታላቅ ድምቀት ከኢትዮጵያ፣ ካውሮፓና ከኖርዌይ የተጋበዙ መምህራን፣ ቀሳውስትና መዘምራን በተገኙበት በማህሌት፣ በመዝሙር፣ በቅዳሴና ታቦተ ንግስ ተከብሮ ዋለ።

ግንቦት 1 ቀን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል

የዘንድሮ 2016 ዓ/ም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በዕለተ ቀኗ በመጪው ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን ከኢትዮጵያ፣ ካውሮፓና ከኖርዌይ የተጋበዙ መምህራን፣ ቀሳውስትና መዘምራን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት በማህሌት፣ በመዝሙር፣ በቅዳሴና ታቦተ ንግስ ይከበራል።

ቤተ ክርስቲያኑ ከዋዜማው ረቡዕ ሚያዚያ 30 ቀን 2016 ዓ/ም ከምሽቱ 20:00 ሰዓት ጀምሮ ከኢትዮጵያ በሚመጡት መምህር መጋቤ ሐዲስ ነቅዓጥበብ ከፍያለው በትምህርትና ስብከተ ወንጌል ተጀምሮ የማህሌት፣ የመዝሙር፣ የቅዳሴና ታቦተ ንግስ መርሃ ግብሩ በተከታታይ እስከ ሚቀጥለው ግንቦት 1 ቀን ድረስ ይከናወናል።

በኦስሎና አካባቢው የምትገኙ ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት ተገኝታችሁ የበዓሉና የበረከቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ የደብሩ የሰባካ መንፈሳዊ አስተዳደር በማክበር ይጋብዛል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት በተመለከተ “ልደታ ለማርያም ከዕሴይ ስር በትር ትወጣለች” በሚል አስተምሮ ዘተዋህዶ ገጽ ላይ የተቀመጠውን ትምህርት እዚህ ላይ በመጫን ይመልከቱ።

 

እንኳን ለ2016 ዓ/ም የጌታችንና የመድሃንታችን የእየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረዶ በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን አወጀላቸው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ በታላቅ ኃይልና ሥልጣንም ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ “ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ሆነ” በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲሁም ምዕመናንና ምዕመናት ሰላምታ ከመለዋወጥ አስቀድሞ ይህን ቃል በመናገር የትንሣኤውን አዋጅ ማወጅና መመስከር ይገባቸዋል፡፡

በዘመኑ የነበሩት የካሕናት አለቆች፣ ጸሃፍትና ፈሪሳዊያን ግን በድርጊታቸው ሳይጸጸቱና ሳያፍሩ የክርስቶስን ድል አድራጊነት ከመቀበልና ንሰሃ ከመግባት ይልቅ ትንሳዔውን ለመደብቅና ለመካድ በሀሰት ወሬዎች መጠቀምን መረጡ (ማቴ 28:11)።

 

ዕለተ ቀዳሚት ሥዑር

በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ ‹‹ቀዳሚት ሥዑር›› ትሰኛለች፡፡ ‹‹ቀዳሚት ሥዑር›› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ዕለቱን በተመለከተ ከዚህ በፊት በመምህር ዘበነ ለማ የተሰጠውን ትምህርት ከዚህ በታች የተቀመጠውን ትምህርት ያድምጡ።

የዘንድሮን የትንሳዔ በዓል ምክንያት በማድረግ በዋዜማው ቅዳሜ ሚያዚያ 26 ቀን 2016 ዓ/ም (04. mai 2024) ከምሽቱ 20:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 0300 ሰዓት ድረስ የማህሌት፣ የዝማሬና የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ ለትራንስፖርት እንዲያመች ቤ/ክርስቲያኑ እስክ ጠዋቱ 06:00 ሰዓት ድረስ ከፍት ሆኖ ይሆናል።

በኦስሎና አካባቢው የምትገኙ ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት በመገኘት የበዓሉና የበረከቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ የደብሩ መንፈሳዊ አስተዳደር ይጋብዛል፡፡

የሰሙነ ሕማማት አምስተኛው ቀን ዕለተ ዓርብ”ስቅለት”

ዕለተ ዓርብ እኛ የሰው ልጆች በኃጢአት ቁራኝነት እንኖርበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመባትና ፍጹም ድኅነት ያገኘንባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ ማቴ.27-35-75፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ “አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት»(1ቆሮ.1-18)” እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያን በዕለተ ዓርብ ቀኑን በሙሉ በቤ/ክርስቲያን በመሰባሰብ የክርስቶስን ሕማሙን፣ ስቃዩን፣ ስቅለቱንና ሞቱን በስግደትና በጸሎት ይዘክራሉ፡፡
በዚሁ መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን ለዚሁ አገልግሎት አርብ 03/05-2024 ከጠዋቱ 07:00 ሰዓት ጀምሮ ክፍት ሆኖ ይውላል።
ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ የደብሩ መንፈሳዊ አስተዳደር ይጋብዛል።

ጸሎተ ሐሙስ/ ህጥበተ እግር

ጸሎተ ሐሙስ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ቀን በመሆኑ “ጸሎተ ሐሙስ” ይባላል (ማቴ. ፳፮፥፴፮–፶፮)፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባንም በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ “የምሥጢር ቀን” ይባላል ሉቃስ 22፥14-20፡፡ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ዮሐንስ ወንጌል -13:4-17 ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዅሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መኾኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ በተጨማሪም “ሕጽበተ ሐሙስ ወይንም ሕጽበተ እግር” ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት “የእኛን የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን” ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡
በዓሉ ሓሙስ ሚያዚያ 24 ቀን (02. mai 2024) ከጠዋቱ 08:00 ሰዓት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን (Caspar Storms vei 12, 0664 Oslo) በስግደት፣ በጸሎት፣ በሕጽበተ እግር እና በቅዳሴ ሥነ ስርዓት ተከብሮ ይውላል፡፡ የቅዳሴው ሥነ ስርዓት ከሕጽበተ እግር በኋላ ከቀኑ 12:00 ላይ ይጀምራል።  ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ የደብሩ መንፈሳዊ አስተዳደር ይጋብዛል፡፡