ጾመ ነነዌ!

የነነዌ ከተማ አስቀድሞ በአሦር አማካይነት ከጤግሮስ ወንዝ በስተምሥራቅ (በአሁኗ ኢራቅ ሞሱል ከተማ አቅራቢያ) ተመሠረተች (ዘፍ 10፡11-12)፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ የንጉሥ ሰናክሬም መቀመጫ ሆነች (2ኛ ነገ 19፡36)፡፡ በዚያን ዘመን ነነዌ በአካባቢው ካሉት ታላላቅ ከተሞች አንዷ ነበረች፡፡

በዚያን ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ክፋታቸው ከእግዚብሔር ዘንድ ደርሶ ስለነበር እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ወደዚያ ላከው፡፡ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።” ብሎ ላከው፡፡ ዮናስ ግን ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ቢሞክርም እግዚአብሔር በድንቅ ተአምራቱ ወደ ነነነዌ መልሶታል፡፡ እንደገናም እግዚአብሄር ለዮናስ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት አለው።” ዮናስም ሄዶ “ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች!” ብሎ ጮኸ፣ ሰበከ!

የነነዌ ሰዎችም ፈጥነው ንስሐ ገቡ፡፡ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።” እግዚአብሔርም ምህረቱን ላከላቸው፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።” በዚህ ዘመን ፈጥነው ንስሐ በመግባታቸው ከጥፋት ድነዋል፡፡ ሙሉ ታሪኩን በትንቢተ ዮናስ ከምዕራፍ 1 እስከ 4 ላይ አንብቡት።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ነነዌ ሰዎች “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” ሲል ተናግሯል (ማቴ 12፡41 ሉቃ 11፡32)፡፡ ይህ አስደናቂ ቃል ነው፡፡ ለመሆኑ እነዚህ የነነዌ ሰዎች ስለምንድን ነው “በዚህ ትውልድ ላይ ይፈርዱበታል” የተባለው? ይህ የሚሆነው ስለሚከተሉት አራት ምክንያቶች ነው፡፡

1. የነነዌ ሰዎች በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አመኑ፤ አይሁድ ግን ብዙ ነቢያትና ሕግጋት እያላቸው አላመኑም፡፡
1.1. እንደ እናንተ ብዙ ነቢያት ሳይላኩልን በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አምነን ንስሐ ገብተናል ሲሉ የነነዌ ሰዎች በአይሁድ ላይ ይመሰክሩባቸዋል፡፡
2. የነነዌ ሰዎች የነቢዩ ስበከት አምነው ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን በነቢያት ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት እንኳን አላመኑም፡፡
2.1. እኛ መልእክተኛውን ተቀብለን ንስሐ ስንገባ እናንተ ግን የመልእክተኛውን ጌታ አልተቀበላችሁም ሲሉ የነነዌ ሰዎች በአይሁድ ላይ ይመሰክሩባቸዋል፡፡
3. የነነዌ ሰዎች ምንም ተአምራትን ሳያዩ ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን እጅግ ብዙ ተአምራትን እያዩ ልባቸው ደነደነ፡፡
3.1. የነነዌ ሰዎች እኛ አንድ ተአምር እንኳን ሳናይ አምነን ንስሐ ገብተናል፤ እናንተ ግን እጅግ ብዙ ተአምራት በፊታችሁ ሲደረግ እያያችሁ አምናችሁ ንስሐ አልገባችሁም ብለው ይመሰክሩባቸዋል፡፡ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች፣ ምልክት ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በቀር አይሰጣትም” ማቴ. 16፡4 ብሎ ጌታችን የተናገረው ብዙ ተአምራትን አይተው ለማያምኑ ለእንደዚህ አይነቱ ትውልድ ነው፡፡
4. የነነዌ ስዎች በጥቂት ቀናት ስብከት ብቻ ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን በብዙ ዓመታት ስበከት ንስሐ አልገቡም፡፡
4.1. ስለዚህ የነነዌ ሰዎች እኛ በጥቂት ቀናትና በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አምነናል ንስሐም ገብተናል እናንተ ግን ለብዙ ዘመናት ብዙ ነቢያት ኋላም ጌታ ራሱ ለዓመታት ቢያስተምሯችሁም አምናችሁ ንስሐ አልገባችሁም ሲሉ ይመሰክሩባቸዋል፡፡

ምንጭ፣ Posted on January 26, 2018 by Astemhro Ze Tewahdo

ሦስት ቀናት የሚጾመው ይህ ጾም የነነዌን ሕዝብ ከጥፋት መመለስ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲሁም የነቢዩ ዮናስን የዋህነት ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ የነነዌ ታሪክ የጾምን እና የንሰሃን ፍጹም ኃይል እና ዋጋ የሚያስተምረን ነውና ይህንኑ እያሰብን ጾመን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን! የሃገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት ይጠብቅልን!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚጀመረውን ጾመ ነነዌ በማስመልከት ያስተላለፉትን አባታዊ ቃለ በረከት እዚህ ላይ በመጫን ያንብቡ፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ኪዳነ ምህረት ዓመታዊ የንግስ ክብረ በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ዋለ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት በየዓመቱ የካቲት 16 ቀን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም ዓመታዊ መታሰቢያ ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀት  ይከበራል ።  እመቤታችን ከጌታችን መቃብር በመሄድ ልጄ ወዳጄ ሆይ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ መትተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ በአለች ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ መቃብራት ተሰነጣጠቁ ጌታችንም እልፍ ከእልፍ መላዕክቱ ጋር መጥቶ ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ አላት፡፡ እርሷም መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለ ስሜ ለችግረኛ የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን መባዕ የሰጠውን ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡ ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበ አቡየ ሕያው ወበመንፈስ ቅዱስ ብሎ ቃል ገብቶላት አርጓል፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን ከመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ቀን እና የቃል ኪዳን ፍጻሜ የተከናወነበት ዕለት ሰለሆነ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ርዕሰ ኪዳናትም  ይባላል። ቅዱሳት መጻሀፍት ታሪክ እንደምንማረው በብለይኪዳን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከቅዱሳን ወዳጆቹ የፈጸማቸው አምሰት ልዩ ልዩ ኪዳናት ተከናውነዋል እነዚህም

1- ኪዳነ አዳም: አዳም ሕግን በመጣሱ በሰራው ጥፋት እያዘነ ፈጣሪውን ይቅርታ ቢጠይቅ ከአምስተ ቀን ተኩል በኃላ ከልጅልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው የምህረት ተስፋን ሰጠው። ዘመኑም ሲደርስ የአዳም ተስፋ ከሆነች ከቅድስተ ቅዱሳን ከድንግል ማርያም እግዚአብሔር ወልድ በቤተልሔም ተወለደ ዓለሙንም አዳነ ።

2- ኪዳነ ኖኅ: ምደርቱንም ዳግመኛ በንፍር ውኃ እንደማያጠፋት በስሙ ማለለት ይህም እስከዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል። ዘፍ 9፥8-17

3- ኪዳነ አበርሃም: አብርሃም አባታችን ከሚኖርበት ሀገሩን ቤተሰቡን ትቶ እንዲወጣ  ከእግዚአብሔር ቢታዘዝ እርሱም ፈቃደኛ በመሆን ወደ ማያውቀውሀገርሲሰደድበልቡየታመነውከአምለኩየተቀበለውየተስፋቃልኪዳንይዞነበር።የቃልኪዳንምልክቱም<<ከእናንተወንድሁሉይገረዝየቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ በእኔ እና በእናንተመካካልላለው ቃል  ኪዳንምልከክት ይሆናል ።–ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላላም ቃል ኪዳን ይሆናል ።>>በማለት አብርሃምን ከወገኖቹ ጋር የእግዚአብሔር ሕዝብ ለርስቱ የተለየ የተመረጠ እንዲሆኑ አድርጓል።

4- ኪዳነ ሙሴ: ይህ ኪዳን ለሊቀ ነቢያት ሙሴ የተሰጠ ሲሆን ሕዝቡትዕዛዘ እግዚአብሔርን እንዲጠብቁ እና ከእርሱ ሌላ አምላክ እናዳያመልኩ መመሪያ ይሆናቸው ዘንድ በነብዪ አማካኝነት የመጀመሪያቱን ጽላት በመስጠት ቃል ኪዳኑን  አጽንቷል። ዘጸ24፥1-20

5- ኪዳነ ዳዊት: ይህ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ከተፈጸሙት ዐበይት ኪዳናት አንዱ ሲሆን ከእረኝነት አንስቶ የመረጠው እግዚአብሔር በታናሽነቱ ህዝበ  እስራኤልን ይመራ ዘንድ የመረጠው በትረ መንግሥትን ከቤቱ ለዘላዓለም እንዳማይጠፋ ቃል ኪዳን ገብቶለታል መዝ131፥11-13

በዓሉ በዕለተ ቀኗ ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ/ም (24. februar 2023) ከጠዋቱ 07:00 ሰዓት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴ፣ በስብከትና በመዝሙር በደማቅ ሁኔታ ተክብሮ አልፏል ።

ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን! ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ አትለየን!

ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ በዛሬው ዕለት በደብራችን እና በመላው ኖርዌይ ለሚያገለግሉ አራት ደቀ መዛሙርት የዲቁና ሥልጣነ ክህነትን ሰጡ።

ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የምሥራቅ ጎጃም እንዲሁም የጀርመንና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ/ም በደብራችን ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በመገኘት በመላዋ ኖርዌይ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለሚያገለግሉ አራት ደቀ መዛሙርት የዲቁና ሥልጣነ ክህነት ሰጥተዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ በነገው ዕለት በደብራችን ተገኝተው በኖርዌይ ተወልደው፣ ተምረው ደቀ መዛሙርት ለሚሆኑ ልጆቻችን ሥልጣነ ክህነትን ይሰጣሉ።

አባታችን ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ በኢ.ኦ.ተ.ቤ. የምስራቅ ጎጃም እንዲሁም የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ በጎ ፈቃድ በደብራችን በማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው በነገው ዕለት የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ/ም (18. februar 2024) በኖርዌይ ሃገር ተወልደው፣ ተምረው ለዲቁና ለደረሱ ደቀ መዛሙርት ለሚሆኑ ልጆቻችን ሥልጣነ ክህነትን ይሰጣሉ።

በኦስሎ እና አካባቢው የምትገኙ ምዕመናን እና ምዕመናት በተጠቀሰው ቀን እና ቦታ ከጠዋቱ 06:00 ሰዓት ጀምሮ በመገኘት መርሃ ግብሩን እንድትሳተፉ እንዲሁም ከብፁዕነታቸው ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ትቀበሉ ዘንድ የደብሩ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።