የዘንድሮ 2017 ዓ/ም ጾመ ነነዌ!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዘንድሮን የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ መግለጫ ሙሉ መልእክት እዚህ ላይ በመጫን ያንብቡ፡፡
የዘንድሮ የነነዌ ጾም ከነገ የካቲት 03 ቀን 2017 (fra 10. febryar 2025) ጀምሮ ይጾማል። ሦስት ቀናት የሚጾመው ይህ ጾም የነነዌን ሕዝብ ከጥፋት መመለስ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲሁም የነቢዩ ዮናስን የዋህነት ያስረዳናል፡፡

የነነዌ ከተማ አስቀድሞ በአሦር አማካይነት ከጤግሮስ ወንዝ በስተምሥራቅ (በአሁኗ ኢራቅ ሞሱል ከተማ አቅራቢያ) ተመሠረተች (ዘፍ 10፡11-12)፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ የንጉሥ ሰናክሬም መቀመጫ ሆነች (2ኛ ነገ 19፡36)፡፡ በዚያን ዘመን ነነዌ በአካባቢው ካሉት ታላላቅ ከተሞች አንዷ ነበረች፡፡

በዚያን ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ክፋታቸው ከእግዚብሔር ዘንድ ደርሶ ስለነበር እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ወደዚያ ላከው፡፡ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።” ብሎ ላከው፡፡ ዮናስ ግን ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ቢሞክርም እግዚአብሔር በድንቅ ተአምራቱ ወደ ነነነዌ መልሶታል፡፡ እንደገናም እግዚአብሄር ለዮናስ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት አለው።” ዮናስም ሄዶ “ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች!” ብሎ ጮኸ፣ ሰበከ!

የነነዌ ሰዎችም ፈጥነው ንስሐ ገቡ፡፡ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።” እግዚአብሔርም ምህረቱን ላከላቸው፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።” በዚህ ዘመን ፈጥነው ንስሐ በመግባታቸው ከጥፋት ድነዋል፡፡ ሙሉ ታሪኩን በትንቢተ ዮናስ ከምዕራፍ 1 እስከ 4 ላይ ይገኛል።

ስለዚህ የነነዌ ታሪክ የጾምን እና የንሰሃን ፍጹም ኃይል እና ዋጋ የሚያስተምረን ነውና ይህንኑ እያሰብን ጾመን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ እንዲሁም በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን! የሃገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት ይጠብቅልን!