“መጻጉ” የዐቢይ ጾም 4ኛ ሳምንት

የዐቢይ ፆም አራተኛው ሳምንት መጻጉዕ ይባላል፡፡ ይህ ዕለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም በዚህ ዕለት ስለ ጌታችነ ገቢረ ተዓምራትና ስለ ድውያን ፈውስ በሰፊው ታስተምራለች። መጻጉ በቤተ ሳይዳ የጸበል መጠመቂያ ቦታ ለ38 ዓመት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ለመዳን በተስፋ ሲጠባበቅ የነበረ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ብዙ ዘመን ተኝቶ እንደኖረ አውቆ «ልትድን ትወዳለህን?» አለው፡፡ እርሱም መጠቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም በማለት መልስ ሰጠ፡፡ ጌታችን የሁሉም መድኃኒት በመሆኑ ወዲያው ‹‹ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ሲለው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ። የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5: 1-15 ። ይህንን በተመለከተ በዶ/ር ቀሲስ ዘበነ ለማ ከዚህ በፊት የተሰጠውን ትምህርት ከዚህ በታች በተቀመጠው ቪዲዮ ያድምጡ።

“ምኩራብ” የዐቢይ ጾም 3ኛ ሳምንት

የዐቢይ ጾም 3ኛ ሳምንት ስያሜ “ምኩራብ” ይባላል። “ምኩራብ” ማለትም ቀጥተኛ ፍችው ኮረብታ፣ ተራራ የሚያኸል ታላቅ ሕንጻ ማለት ሲሆን ከዚህም የተነሣ የአይሁድ ቤተ ጸሎት ምኩራብ በመባል ይታወቃል። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ፣ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ስያሜ ነው።
“ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና። “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት” አላቸው።” ማቴ 21፡12-13

የዕለቱ ምስባክ: “የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና። ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ።” መዝሙረ ዳዊት – ምዕራፍ 69:9-10

ይህንን በተመለከተ በዶ/ር ቀሲስ ዘበነ ለማ ከዚህ በፊት የተሰጠውን ትምህርት ከዚህ በታች በተቀመጠው ቪዲዮ ያድምጡ።

የዐብይ ጾም ሁለተኛው ሰንበት “ቅድስት”

የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሰንበት ኢትዮያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደሰየመው “ቅድሰት” ይባላል። ቅድስት ማለት ልዩ፣ ጽኑዕ፣ ክቡር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ስለሆነም በመልኩና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረንን እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ይፈለጋል፡፡ “ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1:15-16፡፡ ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፣ ይሰበካል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱንና ሳምንቱን ስለ ቅድስና ታስተምራለች፡፡ ይህንን በተመለከተ በዶ/ር ቀሲስ ዘበነ ለማ ከዚህ በፊት የተሰጠውን ትምህርት ከዚህ በታች ያለውን ቪዲዮ ይመልከቱ።

የዕለቱ ምስባክ “እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። ምስጋናና ውበት በፊቱ፥ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።” መዝ 96:5-6

የዕለቱ ወንጌል “ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 6: 16

 

እንኳን ለታላቁ ዐብይ ጾም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማት አንዱ የዐቢይ ወይንም የሁዳዴ ጾም ነው። የዘንድሮ የዐቢይ ጾም ከሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ/ም (11. mars 2024) ጀምሮ ለ55 ቀናት ይጾማል፡፡ ይህ ጌታችንና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ በገዳም ገብቶ የጾመው የአርባ ቀንና የአርባ ሌሊት ጾም ምሳሌ ነው፡፡ በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙት 8 ሣምንታት ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደሰየመው የየራሳቸው የሆነ ስያሜና ትርጉም አላቸው። በዚሁም መሰረት የዓቢይ ጾም መግቢያ የሆነው የመጀመሪያው እሁድና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ያለው የሚቀጥለው ሳምንት “ዘወረደ” ይባላል፡፡ ዘወረደ የምስጢረ ሥጋዌ ትምህርት ነው። ማለትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መውረዱን፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን እና በፍጹም ተዋሕዶ ሰው መሆኑን የሚያመለክተው የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ስለሆነ ነው፡፡ የዓብይን ፆም 8ቱ ሳምንታት ስያሜዎች በተመለከተ ከዚህ ቀደም በመምህር ዶ/ር ዘበነ ለማ የተሰጠውን አጭር ማብራሪያ ከዚህ በታች ያለውን ቪዲዮ በመጫን ይመልከቱ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዘንድሮን የዓቢይ ጾም መግባትን አስመልክተው የሰጡትን መግለጫ እዚህ ላይ በመጫን ይመልከቱ።