ሰሞነ ህማማት

ከሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ የዘንድሮው ሰሞነ ህማማት ክሰኞ ሚያዚያ 21 ቀን 2016 ዓ/ም (29. april 2024) ይጀምራል።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራና ፍዳ በማስታወስ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት፣ ከሌላው ቀናትና ጊዚያት በተለየ መልኩ አምላካቸውን የሚማፀኑበት፣ ጥዋት ማታ አምላካቸውን ደጅ የሚጠኑበት፣ ሀጢያታቸውን በቤተክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ውስጥ ታላላቅ በዓላት ማለትም ጸሎተ ሐሙስ (ህጽበት እግር)፣ ስቅለትና ቀዳም ሥዑር ይገኙበታል። ስለሆነም ምዕመናንና ምዕመናት በቤተ ክርስቲያናችን በወጣው ፕሮግራም መሰረት ከጠዋቱ 07:00 ሰዓት ጀምሮ ቤተ ከርስቲያኑ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ክፍት ሆኖ ይውላል። ምዕመናንና ምዕመናት በቦታው ተግኝታችሁ የአገልግሎቱና የበረከቱ ተካፋዮች እንድትሆኑ የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ ያስታውቃል።

ይህ ሰሞነ ህማማት ከአምላካችን ጋር የምንገናኝበት የንስሀ፣ የጾምና የፀሎት ጊዜ ይሁንልን አሜን!!!

“ሆሳዕና” የዐብይ ጾም ስምንተኛው ሳምንት

የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል ከማክበራችን በፊት ያለው ሰንበት ሆሳዕና ተብሎ ይጠራል፤ በዚህ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ቀን ይዘከራል፡፡ «አንች የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ ንጉሥሽ በእህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል» ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ ዮሐ.12፥ 14-15፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩት ሰዎች በሆሳዕና ቀን ዘምረውና ክርስቶስን አሞግሰው፣ በስቅለተ ዓርብ ቀን (ከአምስት ቀናት በኋላ) ግን «ይሰቀል» ብለው አብዝተው ጮሁ፡፡ በሆሳዕና ቀን «ንጉሣችን» ብለው ዘምረው በስቅለተ-ዓርብ ቀን ደግሞ «ደመኛችን ነው» አሉ፤ ቀድሞ ልብሳቸውን እንዳላነጠፉለትና የተቀመጠባት አህያ እንድተራመድበት እነዳላደረጉ ሁሉ፣ በኋላ የሱን ልብስ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት፤ «ይንገሥ» ባሉበት አንደበት መልሰው «ይሙት»፣«ይሰቀል» ብለው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጮሁ፤ ስለ መሲሕ መምጣት ግድ ያልነበረው ጲላጦስ እንኳ እነሆ ንጉሳችሁ ቢላቸው፣ እንደውም «ከዚህ ሰው ደም ንጹህ ነኝ» ብሎ በፊታቸው እጁን ቢታጠብም በደሉ በእኛ ብቻ ሳይሆን በልጅ ልጆቻችን ላይ ይሁን ብለው በመማማል እንዲሞት አጥብቀው ለመኑ፡፡ የነዚህ ሰዎች እምነት የጸናች አልነበረችምና በዘመኑ በነበሩት የካህናት አለቆች እና መምህራን ሽንገላ ከትክክለኛው መንገዳቸው ወጡ፤ ከኢየሱስ ይልቅ በርባንን መረጡ፡፡ ይህንን በተመለከተ በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው የተሰጠውን ትምህርት እዚህ ላይ በመጫን ያዳምጡ።

በዓሉ ዕሑድ ሚያዚያ 20 ቀን 2016 ዓ/ም  (28. april 2024) ከጠዋቱ 07:00 ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን (Caspar Storms vei 12, 0664 Oslo) በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል፡፡ ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ የደብሩ መንፈሳዊ አስተዳደር ይጋብዛል፡፡

ኒቆዲሞስ – የዐብይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት

በቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ኒቆዲሞስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን ያመለክታል። ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፥ ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ሲሆን በለሊት ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየሄደ ሰለ ሚስጥረ ጥምቀት፣ ሚስጥረ ሥላሴ፣ ሚስጥረ ሥጋዌና ሚስጥረ ትንሳኤ ሙታን መማሩን የሚነገርበት በተለይ ሳምንቱ ስለኒቆዲሞስ ስብእና የሚነበብበት፣ የሚተረጎምበትና የሚሰበክበት ሳምንት ነው። (ዮሐ 3 : 1- 12)
ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን በሥጋዊ ሕይወቱ ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ መሆኑ፣ ልቡናውን ከፍ በማድረግ ከፈሪሳውያን ህብረት ወጥቶ በትህትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል ማዘጋጀቱ፣ በሌሊት በመትጋትና ወደ ጌታ በመሄድ ለትጋት አብነት መሆኑ፣ አይሁድ ጌታችንን ለማሰርና ለመግደል በሚዶልቱበት ወቅት ማንንም ሳይፈራ «…ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?..» (ዮሐ 7-50-52) በሎ በእውነት በመመስከሩ፣ እስከ መጨረሻው በመጽናት በቀራንዮ ተግኝቶ ለክብር መብቃቱ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ከምንማራቸው ቁም ነገሮች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው።

“ገብር ሔር” የዐቢይ ጾም ስድስተኛው ሳምንት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ መሠረት የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ገብር ሔር ይባላል፡፡ ገብር ሔር ማለት ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ታልቅ ትምህርት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25፥14-25 እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሳምንት የተሰጣቸውን ጸጋ አውቀው፣ ተርድተውና ተቀብለው በታማኝነት ኃለፊነታቸውን የተወጡ መልካም አገልጋዮች በጌታቸው ፊት “…አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ…” በመባል መወደሳቸውና መሸለማቸው ይነገራል፣ ይወሳል፣ ይሰበካል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የተሰጠውን ጸጋ ሳያውቅና ሳይረዳ ቸል ብሎ ኃላፊነቱን ያልተወጣ እኩይ ሎሌ በጌታው መወቀሱና መቀጣቱ የሚነገርበት፣ የሚወሳበትና የሚሰበክበት ሳምንት ነው፡፡ ዕለቱን በተመለከተ በመምህር ዶ/ር ዘበነ ለማ ከዚህ በፊት የተሰጠውን ትምህርት ከዚህ በታች ባለው ቪዲዮ ይከታተሉ።

‹‹ደብረ ዘይት›› የዓብይ ጾም አምስተኛ ሳምንት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ቀኖና መሠረት የዓብይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል ይከበራል፡፡ ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ዓለም መጨረሻና ዳግም ምጽአቱ በሚገባ አስተምሯል (ማቴ 24 ፥ 1-36)፡፡ በመሆኑም 5ኛው የዓቢይ ጾም ሰንበት የክርስቶስ ነገረ ምጽአት የሚታሰብበትና የሚሰበክበት ዕለት ስለ ሆነ በደብረ ዘይት ተሰይሟል። የደብረ ዘይት ሰንበት ስለምጽአት የተነገረበት ከመሆኑም በላይ በዚህ ዕለት ምጽአት እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸዉ ወደ እርሱ ቀርበዉ “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነዉ? አሉት።” ለመጀመሪያው ጥያቄ «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም» (ማቴ.24፥.36) ሲል በአጭሩ ሲመልስ ስለ ሁለተኛው ጥያቄ ማለትም ስለምልክቱ ጉዳይ ግን በሰፊው አስተምሯል። ታዲያ የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው? በመምህር ዶ/ር ዘበነ ለማ የተሰጠውን ትምህርት ከዚህ በታች ባለው ቪዲዮ ይከታተሉ።