እንኳን ለዘንድሮ አስተርእዮ ማርያም ክብረ በዓል አደረሳችሁ!!!

“ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአፅብ ለኩሉ”

“ሞት ለሟች ይገባል የማርያም ሞት ግን ለሁሉ ይደንቃል!!!”

ጥር 21 ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት ይታሰባል፡፡

ሞት በአዳም በደል ምክንያት የመጣ ዕዳ ነው፤ባህርያዊ ሳይሆን ባህርያዊ መስሎ ከባህርያችን ጋር ተስማምቶ የሚኖር ፍዳ ነበር፡፡ ሞት ጌታችን ሳይገድለው/ሳይሽረው በፊት ወደ ሲኦል መውረጃ መንገድ ነበር፤ ለአጋንንት እግር እርግጫ፤ ለመንጸፈ ደይን ተመቻቻተን የምንሰጥበት ሂደት፤ ሥጋ በመቃብር የሚፈርስበት፤ ነፍስ በሲኦል የምትሰቃይበት ክስተት ነበር፡፡
ክርስቶስ ሲመጣ ግን ይህ ሞት የሚለው ንባብ ሳይቀየር ትርጉሙና ምሥጢሩ ተቀየረ፤ መጠጫው ጽዋው ሳይቀየር መጠጡን እንደመቀየር ነው፤ መሞት በሐዲስ ኪዳን መሻገር ነው፤ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መጠራት፤ መቃብርም ለትንሣኤ ዘጉባኤ መቆያ ስፍራ ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለምን ሞተች? ሞት የጥንተ አብሶ ውጤት ከሆነ እመቤታችንም የሞተችው ጥንተ አብሶ ስላለባት ነው ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፤ አነዚህ ሰዎች በሐዲስ ኪዳን ሞት ምን እንደሆነ ያለመረዳታቸውና እንዲሁም የእመቤታችን ሞት ምክንያቱ ምንድነው የሚለውን ባለማወቃቸው ምክንያት የሚናገሩት ነው፡፡
ሞት ጥንተ አብሶ ያለበት ብቻ ነው የሚሞተው ከተባለ ጌታችን ራሱ መሞቱ ጥንተ አብሶ ስላለበት ነው ያሰኛል፤ ይህ ደግሞ እርሱ ንጹሕ ሆኖ ሳለ ስለእኛ ሞተ የምንለውን የድኅነት ፅንሰ ሀሳብ ከንቱ ያደርግብናል፤ ስለዚህ ሞት ከክርስቶስ በኋላ የመብቀል ሂደታችን መሆኑን እንመርምር፡፡
ይህን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይነግረናል:—
“አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም”፤ ይላል 1ኛ ቆሮ 15፡36፡፡ ሰለዚህ ሞት በሐዲስ ኪዳን ሕያው ለመሆን የምናልፍበት ሂደት (process) ነው፡፡

ራሱ ጌታችንም ሲያስተምረን:—

“እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም”፤ ዮሐ 5፡24፡፡

ዳግመኛም ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አያይም” ብሏል፤ ዮሐ 8፡51፡፡

ይህም ማለት ነፍስ ከሥጋ አትለይም ማለት አይደለም፤ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ነፍስ በገነት እንደምትኖር፤ ከዚያም በትንሣኤ ዘጉባኤ ጊዜ ነፍሳችን ከሥጋችን ጋር ተዋሕዳ ተነሥተን ከመላእክት ጋር እያመሰገንን የምንኖረውን ዘላለማዊ ሕይወት ለመግለጽ እንጂ፡፡

እመቤታችን ቃሉን በመስማትና በማመን በመጠበቅ የመጀመሪያዋና ተወዳዳሪም የሌላት ናት፤ ማንም ሊሰማው የማይችለውን “ቃል ሥጋ ኮነ” ን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማች መስማት ብቻ ሳይሆን ያመነች ናት፤ ቅድስት ኤልሳቤጥ “ወብፅዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃል ዘነገሩኪ እምኀበ እግዚአብሔር ፤ (ከእግዚአብሔር የተነገረሽ ቃል እንደሚፈጸም ያመንሽ አንቺ ብፅዕት ነሽ) ብላ እንዳመሰገነቻት (ሉቃ 1፡45) “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ብላ ስታምን ነበር ሞትን ያለፈችው፤ ትንሣኤ ልቡናን ቀድማ የተነሣችው፤ ይህ ምሥጢር የተከናወነባት ናት፤ እያንዳንዱን የጌታን ቃል በልብዋ ትጠብቀውና ታስበው እንደነበር ተጽፏል፤ሉቃ 2፡51፡፡

እንዲህ ከሆነ ሕይወት የሆነውን ጌታ ፀንሳ፤ወልዳ የድንግልና ጡት ያጠባች ሆና እንዴት ትሞታለች? ሕይወትን የዳሰሱ እጆች፤ ሕይወትን የተመለከቱ ዓይኖች፤ ሕይወትን ያቀፉ ጉልበቶች እንዴት ለሞት ይሰጣሉ? ብለን ስንጠይቅ የሚከተሉት ምላሾች ይኖሩናል፡፡

– ከተገፋችበት ፤ ከተንከራተተችበትና የኀዘንና የመከራ ሰይፍን ካስታናገደችበት ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ወደመንግሥተ ሰማያት መጠራቷን፤ የማያልፈውን ዋጋ እንደተቀበለች ለማሳየት እንጂ የሞት ሞት የሚባለውን መፍረስና መበስበስን፤ወደ ሲኦል መውረድን የሚያሳይ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ይህንንም ቅዱስ ያሬድ “ደብተራ ፍጽምት ዘጳውሊ ፈለሰት እምዘ ይበሊ ኀበ ኢይበሊ፤ዳዊት አቡሃ በመሰንቆሁ እንዘ የኀሊ፤የሰው እጅ ያልሰራት ድንኳን ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረላት እመቤታችን አባቷ ዳዊት በመሰንቆው እያመሰገናት ከሚያረጀው ዓለም ወደማያረጀው/ወደማያልፈው ሄደች”
በማለት እነደነገረን ነው፡፡

– ከሰማይ የወረደች (ኃይል አርያማዊት) ናት የሚሉ አሉና ሰው እንደሆነች እና ከምድር እንደተገኘች፤ሙሉ የሰውነት ማንነት ያላት መሆኑን ለማጠየቅ ነው፤ እመቤታችንን ሞት ባያገኛት ካልዕ ፍጥረት (ልዩ ፍጥረት) ስለሆነች ነው ብለው ብዙዎች በተከራከሩ ነበር፤ይህም ደግሞ ክርስቶስ የነሣውን ሥጋና ነፍስ (ምሥጢረ ተዋሕዶን) ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተው ነበርና በዚህ ምክንያት በሕገ ሰብእ በሩካቤ ብእሲ ወብእሲት ስለተገኘች በሕገ ሰብእ ሞት ተጠርታለች፤ ይህ ሞቷ እሷን ሌላ ፍጥረት የጌታን ተዋሕዶ ምትሐት ከማለት የሚታደግ መድኃኒትም ጭምር ነው፡፡

– ፍትሑ ርቱዕ (ፍርዱ ቅን የሆነ) እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ ያጠይቃል፤ እመቤታችን እንደማንኛውም ሰው ሞትን ባታይና ባትቀምስ ፍርዱ ትክክል አይደለም፤ አንዱን በሞት ይወስዳል ሌላውን ይተዋል፤ወዲህም ልጅዋ አምላክ ነውና ሞትን ያልቀመሰችው በልጅዋ ምክንያት እንጂ እርሷ የተለየ ቅድስና ስላላት አይደለም በተባለ ነበርና ሞትን እንድትቀምስ ፈቅዷል፤ሞትን መቅመሷ በክብር ላይ ክብር ቢጨምርላት እንጂ ቅንጣት ታህል ክብር አይቀንስባትምና፡፡

ይህንንም ደራሲው፦

“ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ፤ ክርስቶስ ሥጋውን ለነሳበት አካል በሞት አላዳላም” በማለት ተናግሯል፡፡

ቅዱስ ያሬድም ፦

“እንበይነዝ አእምሩ በውስተ ፍትሕ ከመ ኢያደሉ ትጥዓም ሞተ እሙ ወእመ ኩሉ አዘዘ ወልድ በርቱዕ ቃሉ”

(በፍርድ እንደማያዳላ ስለዚህ ነገር ዕወቁ፤የእርሱ እናት፤የሁሉ እናት እመቤታችን ሞትን ትቀምስ ዘንድ ወልድ በማይሻር ቃሉ አዘዘ) በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (የዕለቱ ዚቅ)፡፡

– በነገረ ማርያም ላይ እንደተጻፈው እመቤታችን የዕረፍት ጊዜዋ መድረሱን ጌታችን ሲነግራት እንዴት እኔ የአንተ እናት ሆኜ ሞት ያገኘኛል? በማለት ጠይቃለች፤ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸው “እፎኑመ እመ አምላክ በከየት ደንጊፃ ከመ ኩሉ ሰብእ ሞት ሶበ ሐወጻ፤ እንደማንኛውም ሰው ሞት በጎበኛት ጊዜ የአምላክ እናት እንደምን አለቀሰች?” (የዕለቱ ዚቅ)፡፡
ጌታችንም አንቺ ስትሞቺ ባንቺ ሞት ምክንያት ከሲኦል የሚወጡ ነፍሳት አሉ በማለት ነገራት፤ እመቤታችንም ርኅርኅት ናትና በኔ ሞት ምክንያት ነጻ የሚወጡ ነፍሳት ካሉ አንድ ጊዜ አይደለም ሰባት ጊዜ ልሙት ብላ መልሳለታለች፤ ይህም ማለት ሁሉም ነፍሳት በእመቤታችን ሞት ምክንያት ከገነት ይወጣሉ ማለት ሳይሆን እግዚአብሔር ባወቀ የእናቱ ሞት ቤዛ እንዲሆናቸው የመረጣቸው ነፍሳት መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

• በብሉይ ኪዳን ጥንተ አብሶ ያለባቸው ሰዎች ሲሞቱ መልአከ ሞት ይታያቸው ነበር ለእመቤታችን ግን ልጅዋ ራሱ ክርስቶስ ነው የተገለጠላት፤

• በብሉይ ኪዳን የሞቱ ሰዎች ወደ ሲኦል ነበር የሚወርዱት እመቤታችን ግን ሥጋዋ በገነት ነፍሷ በልጅዋ እጅ ነበር፤

• ከአዳም ልጆች ወገን የመጨረሻውን ትንሣኤ የተነሣ የለም፤እመቤታችን ግን እንደ ልጅዋ ተነሥታለች ዐርጋለች፤መዝ 131፤8፡፡

በመጋቤ ሐዲስ መምህር ነቅዐጥበብ ከፍያለው

መጋቤ ሐዲስ መምህር ነቅዐጥበብ ከፍያለው – የዘንድሮን አስተርእዮ ማርያም ክብረ በዓል በማስመልከት ኖርዌይ ክርስቲያን ሳንድ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤ/ክ “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰) በሚል ርዕስ ያስተማሩትን ድንቅ ትምህርት እዚህ ላይ በመጫን እንድታደምጡ በማክበር እንጋብዛለን።

የመንፈሳዊ ትምህርትና ስብከት መርሃ ግብር በመጋቤ ሐዲስ ነቅዓጥበብ ከፍያለው

በስታቫንገር ደብረ ገነት መድሃኔ አለም ወኪዳነ ምህረት ቤ/ክ የተከበረውን የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ላይ ከኢትዮጵያ ተጋብዘው የተገኙት መምህር መጋቤ ሐዲስ ነቅዓ ጥበብ ከፍ ያለው በነገው ዕለት ዕሑድ ጥር 19 ቀን 2016 ዓ/ም (søndag 28. januar 2023) በደብራችን ማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ ተገኝተው ጥልቅ መንፈሳዊ ትምህርታቸን ያስተምሩናል።

በኦስሎና አካባቢው የምትገኙ ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት ተገኝታችሁ ከማር የጣፈጠ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን እንድትከታተሉ የደብሩ የሰባካ መንፈሳዊ አስተዳደር በማክበር ይጋብዛል።

የጌታችን የመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በስታቫንገር ከተማ በድምቀት ተከብሮ ዋለ!

የጥምቀት በዓል ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁን ለመዘከር የሚከበር በዓል ነዉ፡፡ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ዳግም የምንወለድበት፣የቤተ ክርስቲያን አባል የምንሆንበት፣ የኃጢያት ስርየትና የስጋ ፈውስ የምናገኝበት፣  ነጻነታችን የታወጀበት፣ የዕዳ ደብዳቤአችን የተቀደደበት፣ የባርነት ቀንበር የተሰበረበት፣ ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ረቂቅ ምስጢር ነው።

የዘንድሮ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በድምቀት ተከበረ!

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ!

ቤዛ ኩሉ አለም ዮም ተወልደ / የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ!

የሃይማኖት አባቶቻችን «እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ በጥፋቱ ወድቆ የነበረውን ዓለም ያዳነበት ጥበቡ ይደንቃል» ይላሉ፡፡

  • እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። የሉቃስ ወንጌል – ምዕራፍ 2:10-11
  • የፍጥረቱቲ መሪ የትሩፋት ጀማሪ ይሆን ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ ዮሐ. 13፣14፡፡
  • ሕዝብና አሕዛብን አንድ ሊያደርግ እግዚአብሔር ሰው ሆነ፡፡ ገላ. 3፡28፡፡
  • ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ሆነ፡፡ 1ቆሮ. 1፡20፡፡
  • በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ የመጣውን ዲያብሎስን በመስቀሉ ድል ይነሳው ሥልጣኑንም ይገፍፈው ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ ቆላ. 2፡14፡፡
  • ሀብታም ሲሆን፣ እኛ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች እንሆን ዘንድ ስለእኛ ድሀ ሆነ፡፡ 2ቆሮ. 8፡9፡፡
  • አዳምን ወደ ክብር ቦታው ለመመለስ እርሱ ማደሪያ ስፍራ አጥቶ በግርግም /በከብቶች በረት – በበጎች ጉረኖ/ ተወለደ፡፡ ሉቃስ 2፡7፡፡

የዘንድሮን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከዋዜማው ከቅዳሜ ታህሳስ 27 ቀን 2016 ዓ/ም (06. januar 2024) ከምሽቱ 19:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ዕሑድ ጠዋት ድረስ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በስብከት፣ በቅዳሴና ሌሎች በተለያዩ መርሃ ግብሮች በታላቅ ድምቀት ተክብሮ ዋለ፡፡

የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል!

ታህሣስ 19 ቀን በዚህ ቀን የእግዚአብሔር አገልጋዮች፣ የቅዱስ ገብርኤል ወዳጆች የነበሩት ወጣቶች ሰለስቱ ደቂቅ አናንያ (ሲድራቅ) ፤ አዛርያ (ሚሣቅ) ፤ ሚሣኤል (አብድናጎ) ንጉሱ ናቡከደነጽዖር ላሰራው ጣዖት አንሰግድም፣ የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ እቶኑ ሊያድነን ይችላል ብለው በዕምነታቸው ጸንተው የተገኙበት ዕለትና ቅዱስ ገብርኤል ከእሳት ያዳናቸው ዕለት መታሰቢያ በዓል በታላቅ ደስታ የሚከበርበት ቀን ነው። ሙሉ ታሪኩ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 3 ላይ ተጽፎ ይገኛል።

የዘንድሮው የታህሳስ ወር የሊቀ መላዕክት የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በቤተ ክርሥቲያናችን ዓርብ ታህሳስ 19 ቀን (29. desember 2023) ከጠዋቱ 07:00 ሰዓት ጀምሮ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በታቦተ ንግስ እንዲሁም ከቀኑ 12 ሰዓት ጀምሮ በቅዳሴ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል።

ከበዓሉ በረከት ረድኤት ያሳትፈን! የሊቀ መላዕክት የቅዱስ ገብርኤል ጥበቃው፣ አማላጅነቱ፣ በረከትና ረድኤቱ አይለየን!

የሰንበት ት/ቤት

በቅርብ ቀን ይጠብቁን

መርሐ ግብር

ዘወትር ዕሑድ ከጠዋቱ 7 ሰአት ጀምሮ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት፣ የስብከትና የመዝሙር መርሃ ግብር በቤተ ክርሥቲያናችን (Caspar Storms vei 12, 0664 Oslo) ይካሄዳል፡፡ ምዕመናንና ምዕመናት በቦታውና በሰዓቱ በመገኘት የበረከቱ ተካፋይ እንድትሆኑ የደብሩ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ በማክበር ይጋብዛል፡፡

እንዲሁም ዘወትር ዕሑድ ከቅዳሴ በኋላ የሰንበት ት/ቤ ለህጻናት የቋንቋ፣ የመጽሃፍ ቅዱስና የመዝሙር ትምህርት በቤተ ክርሥቲያኑ ውስጥ ስለሚሰጥ ወላጆች ልጆቻችሁን በማምጣት እንድታሳትፉ የሰንበት ትምህርት ቤቱ በማክበር ይጠይቃል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን አባል ይሁኑ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኦስሎ ማሕደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ አባል ለመሆን ይመዘገቡ ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊ አክብሮት ጥሪውን ያቀርባል።

በአባልነት የሚገኝ ጥቅም

ማንኛውም ሰው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ከተጠመቀ በኃላ ክርስቲያን ይሆናል ክርስቲያን የሚሆነው በክርስቶስ በማመን ሲጠመቅ ነው። ከጥምቀትም በኃላ የሚከተሉትን ያገኛል

  • እግዚአብሔር በሚሰጠው የልጅነት ጸጋ የመንግሥቱ ወራሽ ይሆናል፤
  • የበደልን እና የኃጢያትን ሥርየት ይቀበላል፤
  • በቤቱ ልጅና ወራሽ በመሆን ከእርሱ በሆነ ጸጋ የመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተካፋይ ይሆናል፡

በመሆኑም ጥንታዊና ታሪካዊ በሆነች በአንዲት የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ጥላ ሥር በመሆን በአጥቢያችን ከምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ጋር ህብረት ሲኖረው የሚያገኘው የማይቋርጥ ጸጋ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኖርዌይ ኦስሎ የማሕደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ ከላይ ከተገለጸው መንፈሳዊ በረከት በተጨማሪ የሚከተለውን መንፈሳዊ አገልግሎት ትሰጣለች፦

  • ጥምቀት፤ ተክሊል እና ጸሎተ ፍታት
  • የካህናት ምክር
  • ለህጻናትና ለወጣቶች ታሪክን፣ ባህልን፣ ቋንቋንና ክርስቲያናዊ ግብረገብነትን ማስተማር
  • የአባልነት ማስረጃ ለሚያስፈልጋቸውና በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ውስጥ መሳተፍ፤ መመረጥና መመረጥ፤

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማሕደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም አባል ለመሆን ይመዝገቡ ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊ አክብሮት እንጠይቃለን። ለአሰራር ቅልጥፍና በዚሁ ድኅረ ገጽ የሚገኘውን የአባልነት ፎርም በመሙላት ቅጹን ሞልተው በሜይል አድራሻቸን አባሪ በማድረግ ቢልኩልን በቀላሉ መመዝገብ እንችላለን፡፡ በማንኛው የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ጥያቄ ካልዎት መልስ እንሰጣለን።

የመመዝገቢያ ቅጹን ከዚህ ያውርዱ (PDF)

 

ስለ እኛ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ የማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ በጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነትና በእግዚአብሔር ፈቃድ መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ/ም ተመሠረተ፡፡ በወቅቱ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ እንጦስ በቦታው ተገኝተው ቤተ ክርስቲያኑን ባርከውና ቀድሰው መሠረት ከመጣላቸውም በላይ በቀጣይነት ከአንድ ዓመት በኋላ የሊቀ መላኩን የቅዱስ ገብርኤል ጽላት በማስመጣት ለቤ/ክርስቲያኑ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ሲመሰረት 19 ምዕመናንና ምዕመናት በአባልነት ተመዝግበው የነበሩት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአባላት ቁጥር ከ200 በላይ ሆኗል፡፡ ቋሚ ቤ/ክ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ለጊዜው በኪራይ ቀደም ሲል በካምፐን ሜኒሄትስ ሁስና በካምፐን ሺርከ አሁን ደግሞ  በCaspar Storms vei 12, 0664 Oslo, የሰንበት ቅዳሴ፣ የሰንበት ት/ቤትና እንዲሁም የበዓላት መርሃ ግብር ሳይታጎሉ ቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ያልተቋረጠ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ቤተ ክርስቲያኑ ቃለ አዋዲን መሠረት በማድረግ የሚከተለውን መርህ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ፦

  • የቤ/ክርስቲያኑ ዋነኛና ተቀዳሚ መርህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መንፈሳዊ ግብረገባዊነት የታነጸና በፍቅር፣ በወንድማማችነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን
  • ቤ/ክርስቲያኑ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት፣ ዘርና ወገን ጋር ያልተያያዘና ያልወገነ መሆኑን
  • ቤ/ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ አማኝ የሆነ ሁሉ የሚስተናገድበትና የሚገለገልበት መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

የማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ ዕምነት ሥር የተቋቋመ ሲሆን በቃለ አዋዲው መሠረት የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔው ቤተ ክርስቲያኑን በበላይነት እንዲያስተዳድር አንድ ካህን፣ ስድስት ምዕመናን/ምዕመናት የሚገኙበት በየሶስት ዓመቱ በጠቅላላው ጉባዔው የሚመረጥ የአመራር አካል ነው፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔው የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣትና ዓላማና ተግባሩን በተቀናጀ ሁኔታ ለማከናወን እንዲችል በቃለ አዋዲው ምዕራፍ 4 አንቀጽ 16 ላይ በተገለጸው መሠረት የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡