ኒቆዲሞስ – የዐብይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት
በቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ኒቆዲሞስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን ያመለክታል። ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፥ ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ሲሆን በለሊት ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየሄደ ሰለ ሚስጥረ ጥምቀት፣ ሚስጥረ ሥላሴ፣ ሚስጥረ ሥጋዌና ሚስጥረ ትንሳኤ ሙታን መማሩን የሚነገርበት በተለይ ሳምንቱ ስለኒቆዲሞስ ስብእና የሚነበብበት፣ የሚተረጎምበትና የሚሰበክበት ሳምንት ነው። (ዮሐ 3 : 1- 12)
ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን በሥጋዊ ሕይወቱ ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ መሆኑ፣ ልቡናውን ከፍ በማድረግ ከፈሪሳውያን ህብረት ወጥቶ በትህትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል ማዘጋጀቱ፣ በሌሊት በመትጋትና ወደ ጌታ በመሄድ ለትጋት አብነት መሆኑ፣ አይሁድ ጌታችንን ለማሰርና ለመግደል በሚዶልቱበት ወቅት ማንንም ሳይፈራ «…ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?..» (ዮሐ 7-50-52) በሎ በእውነት በመመስከሩ፣ እስከ መጨረሻው በመጽናት በቀራንዮ ተግኝቶ ለክብር መብቃቱ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ከምንማራቸው ቁም ነገሮች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው።