እንኳን ለዳግም ትንሳዔ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የትንሳዔ ዕለት ለአስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከላቸው ተገኝቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ብሎ ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ቶማስ ከሔደበት አገልግሎት ሲመለስ የጌታችንን መነሣትና እንደተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ዐየን ብላችሁ ልትመሰክሩ፣ ልታስተምሩ፣ እኔ ግን «ሰምቼአለሁ» ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ ጌታችን መድኀኔዓለም ክርስቶስ ልክ እንደመጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ ለሁለትኛ ጊዜ ተግልጾላቸዋል። በዚሁም መሰረት ለሁለተኛ ጊዜ ቶማስ ባለበት በግልጥ የታየበት ዕለት ሰለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ዳግም ትንሣኤ በማለት ይህንን ዕለት ታከብረዋለች፡፡

“ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው”። ከዚያም በኋላ ቶማስን ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው። ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም። ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው። (የዮሐንስ ወንጌል – ምዕራፍ 20፥26-29)።

ስለዚህ ይህ ሰንበት የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ «ዳግም ትንሣኤ» ተብሎ ከትንሳዔ ባልተናነሰ መልኩ ይከበራል፡፡