ጸሎተ ሐሙስ/ ህጥበተ እግር
ጸሎተ ሐሙስ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ቀን በመሆኑ “ጸሎተ ሐሙስ” ይባላል (ማቴ. ፳፮፥፴፮–፶፮)፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባንም በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ “የምሥጢር ቀን” ይባላል ሉቃስ 22፥14-20፡፡ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ዮሐንስ ወንጌል -13:4-17 ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዅሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መኾኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ በተጨማሪም “ሕጽበተ ሐሙስ ወይንም ሕጽበተ እግር” ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት “የእኛን የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን” ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡
በዓሉ ሓሙስ ሚያዚያ 24 ቀን (02. mai 2024) ከጠዋቱ 08:00 ሰዓት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን (Caspar Storms vei 12, 0664 Oslo) በስግደት፣ በጸሎት፣ በሕጽበተ እግር እና በቅዳሴ ሥነ ስርዓት ተከብሮ ይውላል፡፡ የቅዳሴው ሥነ ስርዓት ከሕጽበተ እግር በኋላ ከቀኑ 12:00 ላይ ይጀምራል። ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ የደብሩ መንፈሳዊ አስተዳደር ይጋብዛል፡፡