ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳውሎስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ሐምሌ 5 ቀን (12. juli) በአንድ በኩል የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ የሚከበርበት ዕለት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መልካሙን የክርስትና ገድል ተጋድለው ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ቀን በታላቅና በተለየ ሁኔታ ይከበራል። ቅዱሳኑ ሰማዕታትን የተቀበሉበት ቀን የተለያየ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናችን በዓሉን በአንድ ቀን ታከብራለች።
ክርስትናን በማስፋፋት ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት እነዚህ ቅዱሳን አባቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልእክታትን ጽፈዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስምንት ምዕራፎችን የያዘ ሁለት መልእክታትን ሲጽፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ አንድ መቶ ምዕራፎችን የያዘ አሥራ-አራት መልእክታትን ጽፏል።
ለአግልግሎት የጠራቸውም የክብር ባለቤት የሆነው አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ለሐዋርያነት የተመረጠው ጌታችን በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ሆኖ ዓሣ ለማጥመድ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ወደ እነርሱም ቀርቦ “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት፡፡ (ማቴ.፬፥፲፰‐፳)። በአንጻሩ የቅዱስ ጳውሎስ አመራረጥ ደግሞ በተአምር ነው የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 9: 1 – 20፡፡
የቅዱሳኑ በረከት ዘወትር ከእኛ ጋር ይሁን አሜን!
ቅዱሳን ሐዋርያት ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጠብቀን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን እንድንኖር፤ በመጨረሻም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንድንበቃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን!