ጷጉሜ(ጷጉሜን) እንኳን ለትንሿ የበረከት ውርሃ ጳግሜ በሰላም አደረሳችሁ!

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጷጉሜን የወር ተጨማሪ ሳይሆን የዓመት ተጨማሪ በማድረግ ወሮቹን 30 ቀን፣ የዓመቱንም ቀን ቁጥር ደግሞ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን አድርገው ሰይመውታል፡፡ ጷጉሜን የሚለው ስያሜዋ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን “ኤፓጉሜኔ” ማለት ጭማሪ ማለት ነው ፡፡ በግእዝ ቋንቋችን ተውሳክ ማለት ነው፡፡ ተውሳክ ማለት ተጨማሪ ማለት ነው፡፡
በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጷጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡
የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ ፪፡-፪-፯፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡ ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና በመኖር በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ
እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን እንዲያድን ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ ፰፡-፪፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጷጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡
የጷጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጷጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ፣ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፣ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ስለሆነ ነው፡፡
ሊቃውንቱ እንደ ሱባኤ ቀን ቀኖና እንዲፈጽምባት ለብቻ ለይተው አኑረውታል፡፡ “ይህ ዓለም ኑሮ፣ ኑሮ በመጨረሻ ያልፋል፡፡ ጌታ ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል” ሲሉ የጌታ የመምጣቱ ነገር እንዲነገርባት፣ መሥዋዕት እንዲሠዋባት፣ ጾም እንዲያዝባት፣ ምጽዋት እንዲመጸወትባት ለይተው መድበዋታል፡፡
በየዓመቱ በጷጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን፣ መጪውንም ህይወታችን ደግሞ የተባረከ እንዲያደርግልን ንስሐ ገብተን፣ በጾም በጸሎት ብናሳልፍ ጥቅሙ ለእኛው ለራሳችን ነው።፡

የቅዱስ ሩፋኤል በረከት ረድኤት ይድርብን!

መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ (ጷጉሜ) ይሁንላችሁ፡፡