ጾመ_ነቢያት!
እግዚአብሔር አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ መልበሱን፣ ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ ግብጽ ግብር መሰደዱን፣ በባሕረ ዮርዳኖስ መጠመቁን፣ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ማብራቱን፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ልዩ ልዩ ዓይነት መከራ መቀበሉን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ ማረጉንና ዳግም ለፍርድ የሚመጣ መኾኑን በአጠቃላይ የማዳን ሥራውን በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው አስቀደመው በትንቢት ተናግረዋል፡፡ ትንቢቱ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው ኾኖ ዓለምን የሚያድንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎትም በእግዚአብሔር ሰው መኾን ፍጻሜ አግኝቷል፡፡
ይህን ምሥጢር በማሰብ በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ዋይዜማ ድረስ እንድንጾም አባቶቻችን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ ይህ ጾም፣ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሲኾን፣ በስያሜም ጾመ_ነቢያት (የነቢያት ጾም) እየተባለ ይጠራል፡፡ በዚህ በጾመ ነቢያት፣ ነቢያትም ሐዋርያትም፣ ቀደምት አባቶቻችንም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባናል፡፡
ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ ጾመ መድኃኒት ያድርግል፣ ሃገራችንን ሰላም ያድርግልን፣ ሱባዔውን በሰላም በጤና አስፈጽሞ ለብርሃነ ልደቱ በሰላም ያድርሰን!