እንኳን ለታላቁ ዐብይ ጾም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማት አንዱ የዐቢይ ወይንም የሁዳዴ ጾም ነው። የዘንድሮ የዐቢይ ጾም ከሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ/ም (11. mars 2024) ጀምሮ ለ55 ቀናት ይጾማል፡፡ ይህ ጌታችንና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ በገዳም ገብቶ የጾመው የአርባ ቀንና የአርባ ሌሊት ጾም ምሳሌ ነው፡፡ በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙት 8 ሣምንታት ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደሰየመው የየራሳቸው የሆነ ስያሜና ትርጉም አላቸው። በዚሁም መሰረት የዓቢይ ጾም መግቢያ የሆነው የመጀመሪያው እሁድና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ያለው የሚቀጥለው ሳምንት “ዘወረደ” ይባላል፡፡ ዘወረደ የምስጢረ ሥጋዌ ትምህርት ነው። ማለትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መውረዱን፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን እና በፍጹም ተዋሕዶ ሰው መሆኑን የሚያመለክተው የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ስለሆነ ነው፡፡ የዓብይን ፆም 8ቱ ሳምንታት ስያሜዎች በተመለከተ ከዚህ ቀደም በመምህር ዶ/ር ዘበነ ለማ የተሰጠውን አጭር ማብራሪያ ከዚህ በታች ያለውን ቪዲዮ በመጫን ይመልከቱ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዘንድሮን የዓቢይ ጾም መግባትን አስመልክተው የሰጡትን መግለጫ እዚህ ላይ በመጫን ይመልከቱ።