ስለ እኛ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ የማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ በጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነትና በእግዚአብሔር ፈቃድ መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ/ም ተመሠረተ፡፡ በወቅቱ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ እንጦስ በቦታው ተገኝተው ቤተ ክርስቲያኑን ባርከውና ቀድሰው መሠረት ከመጣላቸውም በላይ በቀጣይነት ከአንድ ዓመት በኋላ የሊቀ መላኩን የቅዱስ ገብርኤል ጽላት በማስመጣት ለቤ/ክርስቲያኑ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ሲመሰረት 19 ምዕመናንና ምዕመናት በአባልነት ተመዝግበው የነበሩት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአባላት ቁጥር ከ200 በላይ ሆኗል፡፡ ቋሚ ቤ/ክ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ለጊዜው በኪራይ ቀደም ሲል በካምፐን ሜኒሄትስ ሁስና በካምፐን ሺርከ አሁን ደግሞ በCaspar Storms vei 12, 0664 Oslo, የሰንበት ቅዳሴ፣ የሰንበት ት/ቤትና እንዲሁም የበዓላት መርሃ ግብር ሳይታጎሉ ቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ያልተቋረጠ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ቤተ ክርስቲያኑ ቃለ አዋዲን መሠረት በማድረግ የሚከተለውን መርህ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ፦
- የቤ/ክርስቲያኑ ዋነኛና ተቀዳሚ መርህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መንፈሳዊ ግብረገባዊነት የታነጸና በፍቅር፣ በወንድማማችነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን
- ቤ/ክርስቲያኑ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት፣ ዘርና ወገን ጋር ያልተያያዘና ያልወገነ መሆኑን
- ቤ/ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ አማኝ የሆነ ሁሉ የሚስተናገድበትና የሚገለገልበት መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
የማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ ዕምነት ሥር የተቋቋመ ሲሆን በቃለ አዋዲው መሠረት የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔው ቤተ ክርስቲያኑን በበላይነት እንዲያስተዳድር አንድ ካህን፣ ስድስት ምዕመናን/ምዕመናት የሚገኙበት በየሶስት ዓመቱ በጠቅላላው ጉባዔው የሚመረጥ የአመራር አካል ነው፡፡
የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔው የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣትና ዓላማና ተግባሩን በተቀናጀ ሁኔታ ለማከናወን እንዲችል በቃለ አዋዲው ምዕራፍ 4 አንቀጽ 16 ላይ በተገለጸው መሠረት የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡