ጾመ ነነዌ!

የነነዌ ከተማ አስቀድሞ በአሦር አማካይነት ከጤግሮስ ወንዝ በስተምሥራቅ (በአሁኗ ኢራቅ ሞሱል ከተማ አቅራቢያ) ተመሠረተች (ዘፍ 10፡11-12)፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ የንጉሥ ሰናክሬም መቀመጫ ሆነች (2ኛ ነገ 19፡36)፡፡ በዚያን ዘመን ነነዌ በአካባቢው ካሉት ታላላቅ ከተሞች አንዷ ነበረች፡፡

በዚያን ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ክፋታቸው ከእግዚብሔር ዘንድ ደርሶ ስለነበር እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ወደዚያ ላከው፡፡ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።” ብሎ ላከው፡፡ ዮናስ ግን ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ቢሞክርም እግዚአብሔር በድንቅ ተአምራቱ ወደ ነነነዌ መልሶታል፡፡ እንደገናም እግዚአብሄር ለዮናስ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት አለው።” ዮናስም ሄዶ “ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች!” ብሎ ጮኸ፣ ሰበከ!

የነነዌ ሰዎችም ፈጥነው ንስሐ ገቡ፡፡ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።” እግዚአብሔርም ምህረቱን ላከላቸው፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።” በዚህ ዘመን ፈጥነው ንስሐ በመግባታቸው ከጥፋት ድነዋል፡፡ ሙሉ ታሪኩን በትንቢተ ዮናስ ከምዕራፍ 1 እስከ 4 ላይ አንብቡት።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ነነዌ ሰዎች “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” ሲል ተናግሯል (ማቴ 12፡41 ሉቃ 11፡32)፡፡ ይህ አስደናቂ ቃል ነው፡፡ ለመሆኑ እነዚህ የነነዌ ሰዎች ስለምንድን ነው “በዚህ ትውልድ ላይ ይፈርዱበታል” የተባለው? ይህ የሚሆነው ስለሚከተሉት አራት ምክንያቶች ነው፡፡

1. የነነዌ ሰዎች በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አመኑ፤ አይሁድ ግን ብዙ ነቢያትና ሕግጋት እያላቸው አላመኑም፡፡
1.1. እንደ እናንተ ብዙ ነቢያት ሳይላኩልን በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አምነን ንስሐ ገብተናል ሲሉ የነነዌ ሰዎች በአይሁድ ላይ ይመሰክሩባቸዋል፡፡
2. የነነዌ ሰዎች የነቢዩ ስበከት አምነው ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን በነቢያት ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት እንኳን አላመኑም፡፡
2.1. እኛ መልእክተኛውን ተቀብለን ንስሐ ስንገባ እናንተ ግን የመልእክተኛውን ጌታ አልተቀበላችሁም ሲሉ የነነዌ ሰዎች በአይሁድ ላይ ይመሰክሩባቸዋል፡፡
3. የነነዌ ሰዎች ምንም ተአምራትን ሳያዩ ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን እጅግ ብዙ ተአምራትን እያዩ ልባቸው ደነደነ፡፡
3.1. የነነዌ ሰዎች እኛ አንድ ተአምር እንኳን ሳናይ አምነን ንስሐ ገብተናል፤ እናንተ ግን እጅግ ብዙ ተአምራት በፊታችሁ ሲደረግ እያያችሁ አምናችሁ ንስሐ አልገባችሁም ብለው ይመሰክሩባቸዋል፡፡ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች፣ ምልክት ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በቀር አይሰጣትም” ማቴ. 16፡4 ብሎ ጌታችን የተናገረው ብዙ ተአምራትን አይተው ለማያምኑ ለእንደዚህ አይነቱ ትውልድ ነው፡፡
4. የነነዌ ስዎች በጥቂት ቀናት ስብከት ብቻ ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን በብዙ ዓመታት ስበከት ንስሐ አልገቡም፡፡
4.1. ስለዚህ የነነዌ ሰዎች እኛ በጥቂት ቀናትና በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አምነናል ንስሐም ገብተናል እናንተ ግን ለብዙ ዘመናት ብዙ ነቢያት ኋላም ጌታ ራሱ ለዓመታት ቢያስተምሯችሁም አምናችሁ ንስሐ አልገባችሁም ሲሉ ይመሰክሩባቸዋል፡፡

ምንጭ፣ Posted on January 26, 2018 by Astemhro Ze Tewahdo

ሦስት ቀናት የሚጾመው ይህ ጾም የነነዌን ሕዝብ ከጥፋት መመለስ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲሁም የነቢዩ ዮናስን የዋህነት ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ የነነዌ ታሪክ የጾምን እና የንሰሃን ፍጹም ኃይል እና ዋጋ የሚያስተምረን ነውና ይህንኑ እያሰብን ጾመን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን! የሃገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት ይጠብቅልን!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚጀመረውን ጾመ ነነዌ በማስመልከት ያስተላለፉትን አባታዊ ቃለ በረከት እዚህ ላይ በመጫን ያንብቡ፡፡