የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ዕርገት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያቱ በተለያየ ጊዜ እየተገለጠ ለአገልግሎት ሲያዘጋጃቸው እና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ በ40ኛው ቀን በሐዋርያቱ ፊት አርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው የጌታችን አበይት በዓላት አንዱ ዕርገት ነው። የዘንድሮ የእርገት በዓል ሓሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ/ም (13. juni 2024) ቢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ተከብሮ እልፏል።

በዓለ ዕርገት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ከሚከበሩት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በዓሉ የሚውለው ዕለተ ሐሙስን ሳይለቅ ከበዓለ ትንሣኤ አርባኛው ቀን ላይ ነው። ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ “ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው” ሐዋ. 1:3 በማለት የጻፈውን መሠረት በማድረግ ነው፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ  ዕርገቱ በምድር ላይ የሚሠራውን የትሕትና ሥራ የመፈጸሙ ምልክት ነው፡፡ ዕርገቱም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “በዕልልታና በመለከት ድምፅ ላረገ ለአምላካችን፣ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና አቅርቡ” መዝ 46፥5፡ እንዳለው በታላቅ ክብር እልልታና ምስጋና ነው፡፡