እንኳን ለዘንድሮ አስተርእዮ ማርያም ክብረ በዓል አደረሳችሁ!!!
“ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአፅብ ለኩሉ”
“ሞት ለሟች ይገባል የማርያም ሞት ግን ለሁሉ ይደንቃል!!!”
ጥር 21 ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት ይታሰባል፡፡
ሞት በአዳም በደል ምክንያት የመጣ ዕዳ ነው፤ባህርያዊ ሳይሆን ባህርያዊ መስሎ ከባህርያችን ጋር ተስማምቶ የሚኖር ፍዳ ነበር፡፡ ሞት ጌታችን ሳይገድለው/ሳይሽረው በፊት ወደ ሲኦል መውረጃ መንገድ ነበር፤ ለአጋንንት እግር እርግጫ፤ ለመንጸፈ ደይን ተመቻቻተን የምንሰጥበት ሂደት፤ ሥጋ በመቃብር የሚፈርስበት፤ ነፍስ በሲኦል የምትሰቃይበት ክስተት ነበር፡፡
ክርስቶስ ሲመጣ ግን ይህ ሞት የሚለው ንባብ ሳይቀየር ትርጉሙና ምሥጢሩ ተቀየረ፤ መጠጫው ጽዋው ሳይቀየር መጠጡን እንደመቀየር ነው፤ መሞት በሐዲስ ኪዳን መሻገር ነው፤ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መጠራት፤ መቃብርም ለትንሣኤ ዘጉባኤ መቆያ ስፍራ ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለምን ሞተች? ሞት የጥንተ አብሶ ውጤት ከሆነ እመቤታችንም የሞተችው ጥንተ አብሶ ስላለባት ነው ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፤ አነዚህ ሰዎች በሐዲስ ኪዳን ሞት ምን እንደሆነ ያለመረዳታቸውና እንዲሁም የእመቤታችን ሞት ምክንያቱ ምንድነው የሚለውን ባለማወቃቸው ምክንያት የሚናገሩት ነው፡፡
ሞት ጥንተ አብሶ ያለበት ብቻ ነው የሚሞተው ከተባለ ጌታችን ራሱ መሞቱ ጥንተ አብሶ ስላለበት ነው ያሰኛል፤ ይህ ደግሞ እርሱ ንጹሕ ሆኖ ሳለ ስለእኛ ሞተ የምንለውን የድኅነት ፅንሰ ሀሳብ ከንቱ ያደርግብናል፤ ስለዚህ ሞት ከክርስቶስ በኋላ የመብቀል ሂደታችን መሆኑን እንመርምር፡፡
ይህን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይነግረናል:—
“አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም”፤ ይላል 1ኛ ቆሮ 15፡36፡፡ ሰለዚህ ሞት በሐዲስ ኪዳን ሕያው ለመሆን የምናልፍበት ሂደት (process) ነው፡፡
ራሱ ጌታችንም ሲያስተምረን:—
“እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም”፤ ዮሐ 5፡24፡፡
ዳግመኛም ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አያይም” ብሏል፤ ዮሐ 8፡51፡፡
ይህም ማለት ነፍስ ከሥጋ አትለይም ማለት አይደለም፤ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ነፍስ በገነት እንደምትኖር፤ ከዚያም በትንሣኤ ዘጉባኤ ጊዜ ነፍሳችን ከሥጋችን ጋር ተዋሕዳ ተነሥተን ከመላእክት ጋር እያመሰገንን የምንኖረውን ዘላለማዊ ሕይወት ለመግለጽ እንጂ፡፡
እመቤታችን ቃሉን በመስማትና በማመን በመጠበቅ የመጀመሪያዋና ተወዳዳሪም የሌላት ናት፤ ማንም ሊሰማው የማይችለውን “ቃል ሥጋ ኮነ” ን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማች መስማት ብቻ ሳይሆን ያመነች ናት፤ ቅድስት ኤልሳቤጥ “ወብፅዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃል ዘነገሩኪ እምኀበ እግዚአብሔር ፤ (ከእግዚአብሔር የተነገረሽ ቃል እንደሚፈጸም ያመንሽ አንቺ ብፅዕት ነሽ) ብላ እንዳመሰገነቻት (ሉቃ 1፡45) “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ብላ ስታምን ነበር ሞትን ያለፈችው፤ ትንሣኤ ልቡናን ቀድማ የተነሣችው፤ ይህ ምሥጢር የተከናወነባት ናት፤ እያንዳንዱን የጌታን ቃል በልብዋ ትጠብቀውና ታስበው እንደነበር ተጽፏል፤ሉቃ 2፡51፡፡
እንዲህ ከሆነ ሕይወት የሆነውን ጌታ ፀንሳ፤ወልዳ የድንግልና ጡት ያጠባች ሆና እንዴት ትሞታለች? ሕይወትን የዳሰሱ እጆች፤ ሕይወትን የተመለከቱ ዓይኖች፤ ሕይወትን ያቀፉ ጉልበቶች እንዴት ለሞት ይሰጣሉ? ብለን ስንጠይቅ የሚከተሉት ምላሾች ይኖሩናል፡፡
– ከተገፋችበት ፤ ከተንከራተተችበትና የኀዘንና የመከራ ሰይፍን ካስታናገደችበት ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ወደመንግሥተ ሰማያት መጠራቷን፤ የማያልፈውን ዋጋ እንደተቀበለች ለማሳየት እንጂ የሞት ሞት የሚባለውን መፍረስና መበስበስን፤ወደ ሲኦል መውረድን የሚያሳይ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ይህንንም ቅዱስ ያሬድ “ደብተራ ፍጽምት ዘጳውሊ ፈለሰት እምዘ ይበሊ ኀበ ኢይበሊ፤ዳዊት አቡሃ በመሰንቆሁ እንዘ የኀሊ፤የሰው እጅ ያልሰራት ድንኳን ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረላት እመቤታችን አባቷ ዳዊት በመሰንቆው እያመሰገናት ከሚያረጀው ዓለም ወደማያረጀው/ወደማያልፈው ሄደች”
በማለት እነደነገረን ነው፡፡
– ከሰማይ የወረደች (ኃይል አርያማዊት) ናት የሚሉ አሉና ሰው እንደሆነች እና ከምድር እንደተገኘች፤ሙሉ የሰውነት ማንነት ያላት መሆኑን ለማጠየቅ ነው፤ እመቤታችንን ሞት ባያገኛት ካልዕ ፍጥረት (ልዩ ፍጥረት) ስለሆነች ነው ብለው ብዙዎች በተከራከሩ ነበር፤ይህም ደግሞ ክርስቶስ የነሣውን ሥጋና ነፍስ (ምሥጢረ ተዋሕዶን) ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተው ነበርና በዚህ ምክንያት በሕገ ሰብእ በሩካቤ ብእሲ ወብእሲት ስለተገኘች በሕገ ሰብእ ሞት ተጠርታለች፤ ይህ ሞቷ እሷን ሌላ ፍጥረት የጌታን ተዋሕዶ ምትሐት ከማለት የሚታደግ መድኃኒትም ጭምር ነው፡፡
– ፍትሑ ርቱዕ (ፍርዱ ቅን የሆነ) እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ ያጠይቃል፤ እመቤታችን እንደማንኛውም ሰው ሞትን ባታይና ባትቀምስ ፍርዱ ትክክል አይደለም፤ አንዱን በሞት ይወስዳል ሌላውን ይተዋል፤ወዲህም ልጅዋ አምላክ ነውና ሞትን ያልቀመሰችው በልጅዋ ምክንያት እንጂ እርሷ የተለየ ቅድስና ስላላት አይደለም በተባለ ነበርና ሞትን እንድትቀምስ ፈቅዷል፤ሞትን መቅመሷ በክብር ላይ ክብር ቢጨምርላት እንጂ ቅንጣት ታህል ክብር አይቀንስባትምና፡፡
ይህንንም ደራሲው፦
“ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ፤ ክርስቶስ ሥጋውን ለነሳበት አካል በሞት አላዳላም” በማለት ተናግሯል፡፡
ቅዱስ ያሬድም ፦
“እንበይነዝ አእምሩ በውስተ ፍትሕ ከመ ኢያደሉ ትጥዓም ሞተ እሙ ወእመ ኩሉ አዘዘ ወልድ በርቱዕ ቃሉ”
(በፍርድ እንደማያዳላ ስለዚህ ነገር ዕወቁ፤የእርሱ እናት፤የሁሉ እናት እመቤታችን ሞትን ትቀምስ ዘንድ ወልድ በማይሻር ቃሉ አዘዘ) በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (የዕለቱ ዚቅ)፡፡
– በነገረ ማርያም ላይ እንደተጻፈው እመቤታችን የዕረፍት ጊዜዋ መድረሱን ጌታችን ሲነግራት እንዴት እኔ የአንተ እናት ሆኜ ሞት ያገኘኛል? በማለት ጠይቃለች፤ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸው “እፎኑመ እመ አምላክ በከየት ደንጊፃ ከመ ኩሉ ሰብእ ሞት ሶበ ሐወጻ፤ እንደማንኛውም ሰው ሞት በጎበኛት ጊዜ የአምላክ እናት እንደምን አለቀሰች?” (የዕለቱ ዚቅ)፡፡
ጌታችንም አንቺ ስትሞቺ ባንቺ ሞት ምክንያት ከሲኦል የሚወጡ ነፍሳት አሉ በማለት ነገራት፤ እመቤታችንም ርኅርኅት ናትና በኔ ሞት ምክንያት ነጻ የሚወጡ ነፍሳት ካሉ አንድ ጊዜ አይደለም ሰባት ጊዜ ልሙት ብላ መልሳለታለች፤ ይህም ማለት ሁሉም ነፍሳት በእመቤታችን ሞት ምክንያት ከገነት ይወጣሉ ማለት ሳይሆን እግዚአብሔር ባወቀ የእናቱ ሞት ቤዛ እንዲሆናቸው የመረጣቸው ነፍሳት መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
• በብሉይ ኪዳን ጥንተ አብሶ ያለባቸው ሰዎች ሲሞቱ መልአከ ሞት ይታያቸው ነበር ለእመቤታችን ግን ልጅዋ ራሱ ክርስቶስ ነው የተገለጠላት፤
• በብሉይ ኪዳን የሞቱ ሰዎች ወደ ሲኦል ነበር የሚወርዱት እመቤታችን ግን ሥጋዋ በገነት ነፍሷ በልጅዋ እጅ ነበር፤
• ከአዳም ልጆች ወገን የመጨረሻውን ትንሣኤ የተነሣ የለም፤እመቤታችን ግን እንደ ልጅዋ ተነሥታለች ዐርጋለች፤መዝ 131፤8፡፡
በመጋቤ ሐዲስ መምህር ነቅዐጥበብ ከፍያለው
መጋቤ ሐዲስ መምህር ነቅዐጥበብ ከፍያለው – የዘንድሮን አስተርእዮ ማርያም ክብረ በዓል በማስመልከት ኖርዌይ ክርስቲያን ሳንድ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤ/ክ “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰) በሚል ርዕስ ያስተማሩትን ድንቅ ትምህርት እዚህ ላይ በመጫን እንድታደምጡ በማክበር እንጋብዛለን።