የጌታችን የመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በስታቫንገር ከተማ በድምቀት ተከብሮ ዋለ!
የጥምቀት በዓል ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁን ለመዘከር የሚከበር በዓል ነዉ፡፡ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ዳግም የምንወለድበት፣የቤተ ክርስቲያን አባል የምንሆንበት፣ የኃጢያት ስርየትና የስጋ ፈውስ የምናገኝበት፣ ነጻነታችን የታወጀበት፣ የዕዳ ደብዳቤአችን የተቀደደበት፣ የባርነት ቀንበር የተሰበረበት፣ ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ረቂቅ ምስጢር ነው።
ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን የመሠረተው በሦስት መንገድ ነው።
- መጀመሪያ በተግባር ራሱ ተጠምቆ እንድንጠመቅ አስተምሮናል፤ አርአያም ሆኖናል (ማቴ 3፡13)፡፡
- ሁለተኛም በትምህርቱ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” (ማር 16፡16) እንዲሁም “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ 3፡3-6) በማለት ጥምቀት ለድኅነት አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል፡፡
- ሦስተኛም ለቅዱሳን ሐዋርያት በሰጣቸው ትዕዛዝ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 28፡19-20) በማለት ምስጢረ ጥምቀትን መስርቶልናል። ይህንንም መሠረት በማድረግ ሃይማኖታቸው የቀና ቅዱሳን አባቶች “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት መሠረተ እምነትን ደንግገዋል፡፡
የዘንድሮ የጥምቀት በዓል እንደወትሮው በኖርዌይ ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ አድባራት ማለትም
- የስታቫንገር ደብረ ገነት መድሃኔ አለም ወኪዳነ ምህረት ቤ/ክ
- የኦስሎ ማህደረስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ
- የክርስቲያንሳንድ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤ/ክ
- የበርገን መንበረ ልዑል ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ
- የትሮንድሐይም ምስራቀ ጸሃይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ ታቦታት በጋራ በተሳተፉበት በስታቫንገር ደብረ ገነት መድሃኔ አለም ወኪዳነ ምህረት ቤ/ክ አዘጋጅነት በስታቫንገር ከተማ (Sunde og Kvernevik bydelshus, Traneveien 10, Hafrsfjord) ቅዳሜና ዕሑድ ጥር 11ና 12 ቀን 2016 ዓ/ም (20. og 21. januar 2023) በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ።
በዓሉን በስላም አስጀምሮ ላስፈጸመን ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምሰጋና ይግባው! ከበዓሉ በረከት፣ ረድኤት ያሳትፈን! በዓሉ የበረከት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ያድርግልን!