“ሆሳዕና” የዐብይ ጾም ስምንተኛው ሳምንት

የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል ከማክበራችን በፊት ያለው ሰንበት ሆሳዕና ተብሎ ይጠራል፤ በዚህ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ቀን ይዘከራል፡፡ «አንች የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ ንጉሥሽ በእህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል» ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ ዮሐ.12፥ 14-15፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩት ሰዎች በሆሳዕና ቀን ዘምረውና ክርስቶስን አሞግሰው፣ በስቅለተ ዓርብ ቀን (ከአምስት ቀናት በኋላ) ግን «ይሰቀል» ብለው አብዝተው ጮሁ፡፡ በሆሳዕና ቀን «ንጉሣችን» ብለው ዘምረው በስቅለተ-ዓርብ ቀን ደግሞ «ደመኛችን ነው» አሉ፤ ቀድሞ ልብሳቸውን እንዳላነጠፉለትና የተቀመጠባት አህያ እንድተራመድበት እነዳላደረጉ ሁሉ፣ በኋላ የሱን ልብስ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት፤ «ይንገሥ» ባሉበት አንደበት መልሰው «ይሙት»፣«ይሰቀል» ብለው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጮሁ፤ ስለ መሲሕ መምጣት ግድ ያልነበረው ጲላጦስ እንኳ እነሆ ንጉሳችሁ ቢላቸው፣ እንደውም «ከዚህ ሰው ደም ንጹህ ነኝ» ብሎ በፊታቸው እጁን ቢታጠብም በደሉ በእኛ ብቻ ሳይሆን በልጅ ልጆቻችን ላይ ይሁን ብለው በመማማል እንዲሞት አጥብቀው ለመኑ፡፡ የነዚህ ሰዎች እምነት የጸናች አልነበረችምና በዘመኑ በነበሩት የካህናት አለቆች እና መምህራን ሽንገላ ከትክክለኛው መንገዳቸው ወጡ፤ ከኢየሱስ ይልቅ በርባንን መረጡ፡፡ ይህንን በተመለከተ በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው የተሰጠውን ትምህርት እዚህ ላይ በመጫን ያዳምጡ።

በዓሉ ዕሑድ ሚያዚያ 20 ቀን 2016 ዓ/ም  (28. april 2024) ከጠዋቱ 07:00 ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን (Caspar Storms vei 12, 0664 Oslo) በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል፡፡ ምዕመናንና ምዕመናት በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ የደብሩ መንፈሳዊ አስተዳደር ይጋብዛል፡፡