እንኩዋን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ በዚህች ዕለት ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ከሰይጣን እጅ ያዳነበት ቀን የሚዘከርበት ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው።
ቅዱስ ሚካኤል ሁል ግዜም ስለ ሰው ልጆችና ለነሱም ስለሚበጀው ሁሉ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እየሰገደ ምህረትን ሲለምንና ሲያሰጥ የሚኖር በልዑል እግዚአብሔርና በመላእክት ፊት ታላቅ ሞገስ ያለው መልአክ ነው። ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ – የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ – የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል – ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው።
የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነው?» ብሏል። ዘጸ 15:11።
ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ ፹፭፥፰።
በቅዳሴያችን “ተውህቦ ምሕረት ለሚካኤል፤ ለሚካኤል ምሕረት (ይቅርታ ርኀራኄ) ተሰጠው ይላል፡፡
ነቢዩ ሄኖክም ምሕረት ለሚካኤል መሰጠቱን ገልጿል፡፡ ትሕትናውን ታዛዥነቱን አስረድቷል። መጽሃፈ ሄኖክ 6:5 እንዲሁም መጽሃፈ ሄኖክ 10:12፡፡
ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየወሩ በ12 መታሰቢያውን እንድናደርግ አዘውናል፡፡ ይህንንም ያልቻለ በዓመት አራት ዐበይት በዓላትን ከቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ጀምሮ እንደተቻለ ማዝከር ይገባል፡፡ ወር በገባ በ12 ቀን ከሚከበሩት ዓመታዊ በዓላት መካከል
1. ህዳር 12 ቀን በዚህ ዕለት እግዚአብሔር ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልን በሰማይ ካሉ ሁሉ በላይ አድርጐ ሾመው፡፡ በዚህ ዕለት እንዲሁ ቅዱስ ሚካኤል በታላቅ ክብር ሆኖ በንጉሥ ጭፍራ አምሳል ለነዌ ልጅ ለኢያሱ የታየበት ዕለት ነው፡፡ ኢያሱ 5:13-15
2. ሰኔ 12 በዚህች ቀን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ከሰይጣን እጅ ያዳነበት ቀንና እንዲሁም በዛሬዋ ቀን ጻድቁ ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ ያረፈበት ቀን ነው።
3. ታሀሳስ 12 በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጰያዊው ጻድቅ አባ ሳሙኤል ያረፈበት ቀን ነው።
4. ነሓሴ 12 በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ረድቶ በድል ያነገሠበት ዕለት ነው፡፡
የቅዱስ ሚካኤል ፀሎቱ፣ በረከቱ፣ ረድኤቱና ምልጃው አይለየን !!!