የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል!

ታህሣስ 19 ቀን በዚህ ቀን የእግዚአብሔር አገልጋዮች፣ የቅዱስ ገብርኤል ወዳጆች የነበሩት ወጣቶች ሰለስቱ ደቂቅ አናንያ (ሲድራቅ) ፤ አዛርያ (ሚሣቅ) ፤ ሚሣኤል (አብድናጎ) ንጉሱ ናቡከደነጽዖር ላሰራው ጣዖት አንሰግድም፣ የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ እቶኑ ሊያድነን ይችላል ብለው በዕምነታቸው ጸንተው የተገኙበት ዕለትና ቅዱስ ገብርኤል ከእሳት ያዳናቸው ዕለት መታሰቢያ በዓል በታላቅ ደስታ የሚከበርበት ቀን ነው። ሙሉ ታሪኩ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 3 ላይ ተጽፎ ይገኛል።

የዘንድሮው የታህሳስ ወር የሊቀ መላዕክት የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በቤተ ክርሥቲያናችን ዓርብ ታህሳስ 19 ቀን (29. desember 2023) ከጠዋቱ 07:00 ሰዓት ጀምሮ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በታቦተ ንግስ እንዲሁም ከቀኑ 12 ሰዓት ጀምሮ በቅዳሴ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል።

ከበዓሉ በረከት ረድኤት ያሳትፈን! የሊቀ መላዕክት የቅዱስ ገብርኤል ጥበቃው፣ አማላጅነቱ፣ በረከትና ረድኤቱ አይለየን!