ዜናዎች እና ወቅታዊ ክንውኖች
በአባልነት ለመመዝገብ የምትፈልጉ የአባልነት ፎርምና ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት
የባንክ ሂሳብ ቁጥር፡ 1503 622 909
111030
በቋሚነት
በቋሚነት በየወሩ በቀጥታ በባንክ አካውንት ወይንም በቪፕስ ለመክፈል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የኦስሎ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ የማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ/ክ በጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነትና በእግዚአብሔር ፈቃድ መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ/ም ተመሠረተ፡፡ በወቅቱ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ እንጦስ በቦታው ተገኝተው ቤተ ክርስቲያኑን ባርከውና ቀድሰው መሠረት ከመጣላቸውም በላይ በቀጣይነት ከአንድ ዓመት በኋላ የሊቀ መላኩን የቅዱስ ገብርኤል ጽላት በማስመጣት ለቤ/ክርስቲያኑ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ሲመሰረት 19 ምዕመናንና ምዕመናት በአባልነት ተመዝግበው የነበሩት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአባላት ቁጥር ከ200 በላይ ሆኗል፡፡ ቋሚ ቤ/ክ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ለጊዜው በኪራይ ቀደም ሲል በካምፐን ሜኒሄትስ ሁስና በካምፐን ሺርከ አሁን ደግሞ በCaspar Storms vei 12, 0664 Oslo, የሰንበት ቅዳሴ፣ የሰንበት ት/ቤትና እንዲሁም የበዓላት መርሃ ግብር ሳይታጎሉ ቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ያልተቋረጠ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ፎቶ፦ ብጹዕ አቡነ እንጦስ ቤተክርስቲያናችህንን ባርከው አገልግሎት ሲያስጀምሩ
እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!!
በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሐምሌ 19 የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በዓል ነው፡፡ ይህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሥጋ መከራ እንደታደጋቸው፣ ከፈላ የብረት ጋን እንዳወጣቸውና ከሞት አደጋ እንደታደጋቸው የሚታሰብበት ዕለት ነው። ታሪኩም በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ተመዝግቦ ይገኛል።
“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” መዝ. 33፡7
እንኳን ለአብርሃሙ ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም በጤና አደረሰን አደረሳችሁ!
ሐምሌ 7 ቀን እግዚአብሔር አምላክ፣ የአብርሃሙ ሥላሴዎች በአብርሃም ቤት የገቡበትና ሚስቱ ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ ያበሰሩበት፣ ቸርነታቸውና ፍቅራቸውን የገለጹበት፣ አብርሃምን የባረኩትና መጻዒው ሕይወቱን የነገሩት ዕለት ዕለት ነው፡፡ ዘፍጥረት 18:1-10። ይህ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡
ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳውሎስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ሐምሌ 5 ቀን በአንድ በኩል የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ የሚከበርበት ዕለት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መልካሙን የክርስትና ገድል ተጋድለው ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ቀን በታላቅና በተለየ ሁኔታ ይከበራል። ቅዱሳኑ ሰማዕታትን የተቀበሉበት ቀን የተለያየ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናችን በዓሉን በአንድ ቀን ታከብራለች።
እንኩዋን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላም አደረሳችሁ!
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ 12ቱ ደቀ መዛሙርት፣ 72ቱ አርድእትና 36ቱ ቅዱሳት አንስት በኢሩሳሌም ከተማ በአንድነት ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ በሚያርግበት ጊዜም “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤” ሉቃ 24፥49 ሲል ለሐዋርያቱ በገባላቸው ቃል መሠረት ባረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡
እንኩዋን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ በዚህች ዕለት ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ከሰይጣን እጅ ያዳነበት ቀን የሚዘከርበት ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው።
ቅዱስ ሚካኤል ሁል ግዜም ስለ ሰው ልጆችና ለነሱም ስለሚበጀው ሁሉ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እየሰገደ ምህረትን ሲለምንና ሲያሰጥ የሚኖር በልዑል እግዚአብሔርና በመላእክት ፊት ታላቅ ሞገስ ያለው መልአክ ነው። ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ – የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ – የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል – ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው።
ዓመታዊው የሰንበት ትምህርት ቤት የመዝጊያ መርሃግብርና የወላጆች የትውውቅ ሥነ ሥርዓት
አምና የተጀመረው ዓመታዊው የሰንበት ትምህርት ቤት የመዝጊያ መርሃግብርና የወላጆች የትውውቅ ሥነ ሥርዓት ዝግጅት እንደ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ቅዳሜ ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ/ም (lørdag 15. juni 2024) ከቀኑ 11:30 እስከ 15:00 ሰዓት በላምበረትሴተር ስታዲየም (lambertseter stadion, Glimmerveien 44, 1155 Oslo) በተለያዩ አዝናኝ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ተክብሮ ዋለ።።
“በዘመናችን የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸው።” ሉቃ 16፣8
የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ዕርገት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያቱ በተለያየ ጊዜ እየተገለጠ ለአገልግሎት ሲያዘጋጃቸው እና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ በ40ኛው ቀን በሐዋርያቱ ፊት አርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው የጌታችን አበይት በዓላት አንዱ ዕርገት ነው። የዘንድሮ የእርገት በዓል ሓሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ/ም (13. juni 2024) ቢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ተከብሮ እልፏል።
በዲያቆን ጎርጎርዮስ ደጀኔ ለወጣቶች የሚሰጠው ትምህርት በመቀጠል ዛሬ ቅዳሜ 01. juni ከ16 ሰዓት ጀምሮ እና ነገ ከቅዳሴ በኋላ የመጨረሻው ትምህርት በቤት ክርስቲያናችን ይሰጣሉ።
ወንድማችን ዲያቆን ጎርጎርዮስ ደጀኔ ከአሜሪካ ሀገር መጥቶ የመጀመሪያውን ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ማድረጉ ይታወሳል። ዲያቆን ጎርጎርዮስ በቀጣይነት ዛሬ ቅዳሜ 01. juni ከ16 ሰዓት ጀምሮ እና ነገ ከቅዳሴ በኋላ የመጨረሻ ትምህርት አስተምሮ ወደ መጣበት ይመለሳል። የምትችሉ ሁላችሁ በመገኘት ትምህርቱን እንድትከታተሉ በእግዚአብሔር ስም ጥሪ እናስተላልፋለን።
በደብራችን ማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም የተዘጋጀ ታላቅ ኦርቶድክሳዊ ተዋህዶ የወጣቶች ጉባኤ!
ወጣቱንና ዘመኑን የዋጀ ታላቅ ኦርቶድክሳዊ ተዋህዶ የወጣቶች ጉባኤ መምህር ዲያቆን ጎርጎርዮስ ደጀኔን ከሰሜን አሜሪካ ዴንቨር ኮሎራዶ በመጋበዝ በደብራችን የሚያዘጋጀው ታላቅ የሶስት ቀን የወጣቶች ጉባኤ ከዓርብ ግንቦት 16 እስከ ዕሁድ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ/ም (f.o.m. 24. t.o.m. 26. mai 2024) ድረስ ይካሄዳል።
እንኳን ለዳግም ትንሳዔ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የትንሳዔ ዕለት ለአስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከላቸው ተገኝቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ብሎ ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ቶማስ ከሔደበት አገልግሎት ሲመለስ የጌታችንን መነሣትና እንደተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ዐየን ብላችሁ ልትመሰክሩ፣ ልታስተምሩ፣ እኔ ግን «ሰምቼአለሁ» ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ ጌታችን መድኀኔዓለም ክርስቶስ ልክ እንደመጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ ለሁለትኛ ጊዜ ተግልጾላቸዋል። በዚሁም መሰረት ለሁለተኛ ጊዜ ቶማስ ባለበት በግልጥ የታየበት ዕለት ሰለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ዳግም ትንሣኤ በማለት ይህንን ዕለት ታከብረዋለች፡፡
“ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር ስም ይመስገን እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ነው” መዝ 112:3