ፆመ ፅጌ – ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ እርሱን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜም ጌታችን በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብፅ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታችንን ያገኘው መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ ሀለት ዓመት ከዚያ በታች የሆኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በግፍ አስፈጅቷል፡፡
በተአምረ ማርያምና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ውሃ በጠማቸው ጊዜ ውሃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንን ውሃ ክፉዎች እንዳይጠጡት መራራ ማድረጉ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ሆኖ እንዲቆይ ማድረጉ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ እንደ ቀድሞው ደኅና እንድትሆን ማድረጉ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡