እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

የደብረ ታቦር (የቡሄ) በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤ/ክ ቀኖና መሰረት ከዘጠኙ አብይ በዓላት ውስጥ አንዱ ሲሆን የሚከበረውም ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በማስተማር በነበረበት ጊዜ በደብረ ታቦር ላይ ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግስቱን የገለፀበት ዕለትን ለማስታወስ ነው። ይህ በዐል በየአመቱ ነሃሴ ፲፫ (13) ቀን ይከበራል።
“ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ማቴ 17:1-3

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጾመ ፍልሰታን በማስመልከት መልእክት፣ ቃለ በረከትና ቡራኬ አስተላለፉ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በሀገር ውስጥና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!

በማሕፀነ ማርያም በፈጸመው እውነተኛ ተዋሕዶ የሰው ልጅን ከኃሣር ወደ ክብር የመለሰ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመተ ምሕረት ጾመ ቅድስት ማርያም በደኅና አደረሰን አደረሳችሁ!፤

‹‹ተፈሥሒ ኦ ምልእተ ጸጋ፣ ተፈሥሒ እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር፡- ምልእተ ጸጋ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ በእግዚአብሔ ዘንድ ሞገስን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ›› (ሉቃ. 1÷28-30″)
የክብር አምላክ እግዚአብሔር የሰው ልጅን ከወደቀበት ዐዘቅተ ኵነኔ የሚያድንበት ዕድል እንዳዘጋጀ በብሉይ ኪዳን በስፋት ገልፆል፤ የማዳን ስራውም ከሰው ወገን ከሆነች ቅድስት ድንግል በሚወለደው መሲሕ እንደሚፈጸም አስረድቶአል፤ የማዳን ቀኑ በደረሰ ጊዜም መልእክቱን በፊቱ በሚቆመው በቅዱስ ገብርኤል በኩል ልኮአል፤ ቅዱስ ገብርኤልም የተነገረውን መልእክት ለድንግል ማርያም አድርሶአል፡፡

ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም እንዲነግር ከታዘዘባቸው መካከል ‹‹ጸጋን የተመላሽ ደስተኛይቱ ሆይ÷በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ›› የሚል አስደናቂ መልእክት ይገኝበታል፡፡

ሙሉ መለእክቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ድሀረ ገጽ ላይ ስለሚገኝ ይህንን ሊንክ በመጫን ገብታችሁ እንድታነቡ እናሳስባለን።

እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በስለም አደረሳችሁ፣ አደረሰን አሜን!

ጾመ ፍልሰታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፷፬ ዓመት በዚች ምድር ኖራ እንደ አንድ ልጇ መሞቷን፣ መነሳቷንና ማረጓን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት የጾሙት ጾም ነው። ጾሙን ነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው በነሐሴ አሥራ አራት ቀን ጌታችን እመቤታችንን አምጠቶ እንድትገለጥላቸው አደረገ፤ ቀበሯትም፡፡ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀንም እርገቷን አከበሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን የእመቤታችንን በረከት ለማግኘት ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ነሐሴ ፲፮ ቀን ጾመ ፍልሰታ በመባል ትጾማለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማትም አንዱ ነው። በዚህ ወቅት ምእመናንና ምዕመናት በፆም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት ይማጸናሉ፡፡ ሙሉ ታሪኩን ከዚህ በታች በሚገኘው የአውዲዮ ሊንክ በመጫን አዳምጡ!

ጾሙን ጾመ ደህነት፣ ጾመ በረከት፣ በንሰሀ ተመልሰን ሥጋውና ደሙን ተቀብለን ከእመቤታችን በረከት አግኝተን መንግስቱን ለመወረስ የምንዘጋጅበት ያድርግልን!