እንኳን ለሊቀ መላኩ ቅዱስ ዑራኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን !

ከከበሩ ከመላእክት አንዱ ዑርኤል በመብረቅ በነጐድጓድ የተሾመ ነው። መጽሐፈ ሄኖክ 6:2

ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ በመሆኑም ሐምሌ 22 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበትን ዕለት የሚከበርበትና የሚዘከርበት ዕለት ነው። ጥር 22 በዓለ ሲመቱ ነው። መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ዕለት ነው።

“ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ” መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 2፡1

የቅዱስ ዑራኤል በረከት በሁላችንም ላይ ይደር!! አሜን!

እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!!

በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሐምሌ 19 የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በዓል ነው፡፡ ይህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሥጋ መከራ እንደታደጋቸው፣ ከፈላ የብረት ጋን እንዳወጣቸውና ከሞት አደጋ እንደታደጋቸው የሚታሰብበት ዕለት ነው። ታሪኩም በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ተመዝግቦ ይገኛል።

የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት፣ የሰማዕታቱ የቅዱስ ቂርቆስና ቅዱስ ኢየሉጣ የገድላቸው በረከት ይደርብን!
ሰማዕቱ ቅዱስ ቂርቆስን እና እናቱ ቅድስት እየሉጣን ከፍቱን እሳት ከፈላው ውኃ ያዳንካቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እኛ ልጆችህን አድነን ለሀገራችን ሰላም ለህዝባችን አስተዋይ ልቦናን አድልልን!

የእግዚአብሔር ቸርነት ከሁላችን ጋር ይኑር አሜን!

እንኳን ለአብርሃሙ ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም በጤና አደረሰን አደረሳችሁ!

ሐምሌ 7 ቀን እግዚአብሔር አምላክ፣ የአብርሃሙ ሥላሴዎች በአብርሃም ቤት የገቡበትና ሚስቱ ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ ያበሰሩበት፣ ቸርነታቸውና ፍቅራቸውን የገለጹበት፣ አብርሃምን የባረኩትና መጻዒው ሕይወቱን የነገሩት ዕለት ዕለት ነው፡፡ ዘፍጥረት 18:1-10። ይህ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡

ዛሬም እኛ እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ ለተቸገሩ በመራራትና በመመጽወት፣ ልቡናችንን ንጹሕ በማድረግና ከኀጢአት በመለየት፣ በደግነት፣ በቀና አስተሳሰብ እና በመሳሰለው ተግባር ከኖርን፤ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያድራል፡፡ አድሮም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ እርሱ ያደረበት ሰውነት ይባረካል፣ ይቀደሳልና፡፡ በጥቅሉ የልባችንን መሻት ዐውቆ የምንሻውን መልካም ነገር ሁሉ ይፈጽምልናል፡፡

የአብርሃምን ቤት የባረኩ ቅድስት ሥላሴዎች የእኛንም ቤት በበረክት ይጎብኙን፣ ህይወታችሁን በተስፋ ይምሉልን!!!

ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳውሎስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ሐምሌ 5 ቀን (12. juli) በአንድ በኩል የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ የሚከበርበት ዕለት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መልካሙን የክርስትና ገድል ተጋድለው ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ቀን በታላቅና በተለየ ሁኔታ ይከበራል። ቅዱሳኑ ሰማዕታትን የተቀበሉበት ቀን የተለያየ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናችን በዓሉን በአንድ ቀን ታከብራለች።

ክርስትናን በማስፋፋት ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት እነዚህ ቅዱሳን አባቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልእክታትን ጽፈዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስምንት ምዕራፎችን የያዘ ሁለት መልእክታትን ሲጽፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ አንድ መቶ ምዕራፎችን የያዘ አሥራ-አራት መልእክታትን ጽፏል።

ለአግልግሎት የጠራቸውም የክብር ባለቤት የሆነው አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ለሐዋርያነት የተመረጠው ጌታችን በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ሆኖ ዓሣ ለማጥመድ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ወደ እነርሱም ቀርቦ “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት፡፡ (ማቴ.፬፥፲፰‐፳)። በአንጻሩ የቅዱስ ጳውሎስ አመራረጥ ደግሞ በተአምር ነው የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 9: 1 – 20፡፡

የቅዱሳኑ በረከት ዘወትር ከእኛ ጋር ይሁን አሜን!
ቅዱሳን ሐዋርያት ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጠብቀን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን እንድንኖር፤ በመጨረሻም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንድንበቃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን!