እንኩዋን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ 12ቱ ደቀ መዛሙርት፣ 72ቱ አርድእትና 36ቱ ቅዱሳት አንስት በኢሩሳሌም ከተማ በአንድነት ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ በሚያርግበት ጊዜም “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤” ሉቃ 24፥49 ሲል ለሐዋርያቱ በገባላቸው ቃል መሠረት ባረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡

በሐዋርያት ሥራ እንደ ተጻፈው በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማለዳ ኹሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሳሉ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጣና የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በኹሉም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁላቸውም መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ሁሉ መናገር ጀመሩ ሐዋ 2፥1-4። ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡

“ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ ለኾነው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስሙ ሲኾን፣ ትርጕሙም በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ናዛዚ (የሚናዝዝ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) ማለት ነው፡፡ በዓለ ጰራቅሊጦስ በሌላ ቃል በዓለ ጰንጠቆስጤ በመባልም ይታወቃል፡፡ ይኸውም በግሪክ ቋንቋ በዓለ ሃምሳ፣ የፋሲካ ሃምሳኛ ዕለት፣ በዓለ ሠዊት (የእሸት፣ የመከር በዓል) ማለት ነው። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ 906 እና 907)

 

እንኩዋን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ በዚህች ዕለት ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ከሰይጣን እጅ ያዳነበት ቀን የሚዘከርበት ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው።

ቅዱስ ሚካኤል ሁል ግዜም ስለ ሰው ልጆችና ለነሱም ስለሚበጀው ሁሉ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እየሰገደ ምህረትን ሲለምንና ሲያሰጥ የሚኖር በልዑል እግዚአብሔርና በመላእክት ፊት ታላቅ ሞገስ ያለው መልአክ ነው። ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ – የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ – የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል – ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው።
የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነው?» ብሏል። ዘጸ 15:11።
ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ ፹፭፥፰።
በቅዳሴያችን “ተውህቦ ምሕረት ለሚካኤል፤ ለሚካኤል ምሕረት (ይቅርታ ርኀራኄ) ተሰጠው ይላል፡፡
ነቢዩ ሄኖክም ምሕረት ለሚካኤል መሰጠቱን ገልጿል፡፡ ትሕትናውን ታዛዥነቱን አስረድቷል። መጽሃፈ ሄኖክ 6:5 እንዲሁም መጽሃፈ ሄኖክ 10:12፡፡

ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየወሩ በ12 መታሰቢያውን እንድናደርግ አዘውናል፡፡ ይህንንም ያልቻለ በዓመት አራት ዐበይት በዓላትን ከቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ጀምሮ እንደተቻለ ማዝከር ይገባል፡፡ ወር በገባ በ12 ቀን ከሚከበሩት ዓመታዊ በዓላት መካከል
1. ህዳር 12 ቀን በዚህ ዕለት እግዚአብሔር ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልን በሰማይ ካሉ ሁሉ በላይ አድርጐ ሾመው፡፡ በዚህ ዕለት እንዲሁ ቅዱስ ሚካኤል በታላቅ ክብር ሆኖ በንጉሥ ጭፍራ አምሳል ለነዌ ልጅ ለኢያሱ የታየበት ዕለት ነው፡፡ ኢያሱ 5:13-15
2. ሰኔ 12 በዚህች ቀን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ከሰይጣን እጅ ያዳነበት ቀንና እንዲሁም በዛሬዋ ቀን ጻድቁ ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ ያረፈበት ቀን ነው።
3. ታሀሳስ 12 በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጰያዊው ጻድቅ አባ ሳሙኤል ያረፈበት ቀን ነው።
4. ነሓሴ 12 በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ረድቶ በድል ያነገሠበት ዕለት ነው፡፡

የቅዱስ ሚካኤል ፀሎቱ፣ በረከቱ፣ ረድኤቱና ምልጃው አይለየን !!!

 

ዓመታዊው የሰንበት ትምህርት ቤት የመዝጊያ መርሃግብርና የወላጆች የትውውቅ ሥነ ሥርዓት

አምና የተጀመረው ዓመታዊው የሰንበት ትምህርት ቤት የመዝጊያ መርሃግብርና የወላጆች የትውውቅ ሥነ ሥርዓት ዝግጅት እንደ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ቅዳሜ ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ/ም (lørdag 15. juni 2024) ከቀኑ 11:30 እስከ 15:00 ሰዓት በላምበረትሴተር ስታዲየም (lambertseter stadion, Glimmerveien 44, 1155 Oslo) በተለያዩ አዝናኝ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ተክብሮ ዋለ።።
“በዘመናችን የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸው።” ሉቃ 16፣8

የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ዕርገት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያቱ በተለያየ ጊዜ እየተገለጠ ለአገልግሎት ሲያዘጋጃቸው እና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ በ40ኛው ቀን በሐዋርያቱ ፊት አርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው የጌታችን አበይት በዓላት አንዱ ዕርገት ነው። የዘንድሮ የእርገት በዓል ሓሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ/ም (13. juni 2024) ቢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ተከብሮ እልፏል።

በዓለ ዕርገት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ከሚከበሩት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በዓሉ የሚውለው ዕለተ ሐሙስን ሳይለቅ ከበዓለ ትንሣኤ አርባኛው ቀን ላይ ነው። ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ “ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው” ሐዋ. 1:3 በማለት የጻፈውን መሠረት በማድረግ ነው፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ  ዕርገቱ በምድር ላይ የሚሠራውን የትሕትና ሥራ የመፈጸሙ ምልክት ነው፡፡ ዕርገቱም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “በዕልልታና በመለከት ድምፅ ላረገ ለአምላካችን፣ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና አቅርቡ” መዝ 46፥5፡ እንዳለው በታላቅ ክብር እልልታና ምስጋና ነው፡፡

በዲያቆን ጎርጎርዮስ ደጀኔ ለወጣቶች የሚሰጠው ትምህርት በመቀጠል ዛሬ ቅዳሜ 01. juni ከ16 ሰዓት ጀምሮ እና ነገ ከቅዳሴ በኋላ የመጨረሻው ትምህርት በቤት ክርስቲያናችን ይሰጣሉ።

ወንድማችን ዲያቆን ጎርጎርዮስ ደጀኔ ከአሜሪካ ሀገር መጥቶ የመጀመሪያውን ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ማድረጉ ይታወሳል። ዲያቆን ጎርጎርዮስ በቀጣይነት ዛሬ ቅዳሜ 01. juni ከ16 ሰዓት ጀምሮ እና ነገ ከቅዳሴ በኋላ የመጨረሻ ትምህርት አስተምሮ ወደ መጣበት ይመለሳል። የምትችሉ ሁላችሁ በመገኘት ትምህርቱን እንድትከታተሉ በእግዚአብሔር ስም ጥሪ እናስተላልፋለን።