የህፃናት ጥምቀት
የሕፃናት የ40 ቀንና የ80 ቀን ጥምቀት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሚስጥረ ጥምቀት አፈጻጸም ብርቱ ጥንቃቄ ታደረጋለች፡፡ ሰው ሁሉ በጥምቀት አማካኝነት የሚሰጠውን ጸጋ እንዲያገኝ አሰፈላጊውን ጥረት ሁሉ ትፈጽማለች፡፡
ሰዎች ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ በማለት ሕጻናትን የምታጠምቀው በቅዱሳት መጸሕፍት በተረዳችው መሠረት እንደሆነ ከዚህ ቀጥለን ለማየት እንሞክራለን፡፡
መጽሐፈ ኩፋሌ፡- 4፡9 ከተፈጠረባት ምድር ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኃላ ይገዛትም ይጠብቃትም ዘንድ ወደ ገነት አሰገባው፡፡ ሚስቱንም በሰማንያ ቀን አሰገባት፡፡
ይላልና ለአዳምና ለሔዋን ንጹሕ ጠባይዕ ሳይድፍባቸው ከመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ልጅነት ተቀብለው በ40ና በ80 ቀን ገነት እንድገቡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር መጀመረያ በሠራው ሥራዓት መሠረት በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት የተወሰደውን ልጅነት ለማሰመለሰ ሕጻናት ወንዶችን በ40 ቀን ሕፃናት ሴቶችን በ80 ቀን ዕድሜያቸው ታጠመቃለች፡፡
ሀ, ሕጻናት የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኙ ወላጆቻቸውና ቤተ ክርስቲያን የሚሹት ነው፡፡
የሐ ፡- 3፡5 ሰው ከወኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም፡፡
ስለዚህ ሕጻናት በወላጆቻቸው እምነት የተነሳ የወላጆቻቸውን እምነት የእነርሱ እምነት በማድረግ ገና በሕጻንነት ጊዜያቸው ከእግዚአብሔር መንግስት ውጭ እንዳይሆኑ ታጠምቃቸዋለች፡፡ ዳሩ ግን ሳይጠመቁ ቢሞቱ ጌታ እንደተናገረው መንግስተ ሰማይን አያዩአትም፡፡
እንደ ጌታ ትምህርት የሚንሄድ ከሆነ ሰው ብሎ ባጠቃላይ ሕጻናትን አዋቂዎችን ሁሉ ጨምሮ ተናገረ እንጂ ከሕጻናት በሰተቀር አላለም፡፡ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም፡፡
ለ, ሕጻናት በመጠመቃቸው የቤተ ክርስቲያን አባል ስለሚሆኑ የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ይሆናሉ፡፡
ገና ከሕጻንነታቸው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት ይለማመዳሉ፡፡ በዚህ ፈንታ ከሕጻንነታቸው ጊዜ ጀምረው ከእግዚአብሔር ጸጋ ተራቁተው የሚያድጉ ከሆነ ለመጥፎ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡
ሐ, ለሕጻናት በሚደረግ ጥምቀት መጽሐፍ ቅዱስ አይቃወምም እንደውም ይደግፋል፡፡
ማር ፡- 10፡14 ሕጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው
እንዲሁም ጌታችን ያመነ የተጠመቀ ይድናል ሲል በዚያን ዘመን ገና ወንገል መሰበክ በጀመረበት ላሉት ሰዎች የተነገረ ሲሆን ከክህደታቸውና ከጥርጥራቸው ተመልሰው የሚመጡ ሁሉ አምነው መጠመቅ እንዳለባቸው የሚያሰገነዝብ ነው፡፡ ሕጻናት የእግዚአብሔር ልጆች ሊሆኑ እንደሚገባ ጌታችን ሲገልጽ
ማቴ ፡- 19፡14 ሕጻናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሏቸው መንግሰተ ሰማያት እንደ እነርሱ ላሉት ናትና ብሏል፡፡ በዚህ የጌታ ትምህርት መሠረት ቤተ ክርስቲያንም የመረዋንና የመሥራችዋን የክርስቶስን መርሕ በማድረግ ወላጆቻቸው ታቅፈው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘው በመምጣት ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጆች የቤተ ክርስቲያን አባላት እንዲሆኑ ሲያደረጉ እርሷ ከልካይ አትሆንም፡፡
ጌታ ተዉአቸው ይምጡ ልጅነትን ፤ ጸጋን፤ በረከቱን ያግኙ ብሏልና፡፡
ሕፃናት ንጹሐነ አእምሮ መሆናቸውን ጌታ ሲያሰተምር እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ መንግሰተ ሰማይ አትገቡም ብሏል፡፡
መ, መጽሐፍ ቅዱስ ሕፃናት መጠመቃቸውን ያሰተምረናል፤
1. ሐዋ ፡- 16፡33 በእሥር ቤቱ በተደረገው ተአምር የተደነቀውና ወደ ክርስትና እምነት የተሳበው የወኀኒ ጠባቂ ጳውሎስና ስላስ ካሰተማሩትና ካሳመኑት በኋላ ከነቤተሰቡ መጠመቁ ተገልጾአል፡፡ እንግዲህ የተሰበከውና ያመነው የወኀኒ ጠባቂው ስሆን የተጠመቁት ግን ሕፃናትን ጨምሮ መላው ቤተሰቡ ነው፡፡
2. ሐዋ ፡- 16፡15 ልብዋን ጌታ የከፈተላትና ቃሉን አድምጣ ሕይዋትውን ለክርስቶስ የሰጠችው ልድያ ባመነች ጊዜ የተጠመቀችው ብቻዋን ሳይሆን ከመላው ቤተሰብዋ ጋር ነው፡፡ ከቤተሰቡ መካከል ሕፃናት መኖራቸው የማይቀር ነው፡፡
3. 1ቆሮ ፡- 1፡16 ቅዱስ ጳውሎስ የእስጢፋኖስንም ቤተሰቦች ደግሞ አጥምቄያለሁ በማለት የእስጢፋኖስን መላ ቤተሰብ ማጥመቁን ገልጾአል፡፡ እንዚህ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ሁሉ ትልልቆች ብቻ ናቸውን? ሕጻናት የሉበትም ይሆን?
4. ሐዋ.ሥራ 2 ላይ እንደተገለጸው በበዓለ ሃምሳ ከ3000 ያላነሱ ሰዎች በጴጥሮስ ተሰበኩ፡፡ ከእንዚያ ውስጥ ብዙዎቹ መጠመቃቸው ተገልጸዋል፡፡ የተጠመቁት ግን አዋቂዎች ብቻ መሆናቸውን የሚገልጽ ቃል የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሕጻናትን ጥምቀት የሚነቅፍ ባንዱም ክፍል ተጽፎ አናገኝም፡፡
እስከ አሁን እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ የሕፃናትን ጥምቀት ያልነቀፈ ሲሆን በብሉይ ኪዳን የጥምቀት ምሳሌ የነበሩትን ስንመለከት ይበልጥ የሕጻናትን ጥምቀት ትክክልኛነት ያረጋግጡልናል፡፡
ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናት በተወለዱ በስምነተኛው ቀን ይገረዙ ነበር፡፡ (ዘፍ ፡- 17፡12)፡፡
እንግዲህ ሕፃናቱ የሚገረዙት በወላጆቻቸው እምነት እንጅ እነርሱ ዐውቀው ግረዙን ብለው አይደለም፡፡ የእስራኤል ቀይ ባሕርን ማቋረጥ የጥምቀት ምሳሌ መሆኑ በ1ቆሮ 10፡2 የተገለጸ ስሆን ባሕሩን ያቋረጡት ዐዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናትም ጭምር ናቸው፡፡ ከባርነት ከፈርዖን አገዛዝ ነፃ የወጡት ሕፃናቱም ጭምር ናቸው፡፡ እስራኤል ከቡኩረ ሞት የዳኑበት የአንድ አምት ጠቦት በግ ደግሞ ምሳሌነቱ የጌታ መሆኑ የተወቀ ስሆን በዚያን ጊዜ በበጉ ደም አማካኝነት ከሞት የዳኑት የታዘዙትን እሺ ብለው የፈጸሙት ዐዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የእነርሱም ልጆቹም ጭምር ናቸው፡፡ እንግዲህ በወላጆቻቸው እምነት ሕፃናቱ መዳናቸውን ልናሰተውል ይገባል፡፡
ስለዚህ ሕፃናት በአእምሮ ባለበሰሉበትና ስለጥምቀታቸው አምነው ተቀብያዋለሁ ሳይሉ የሚደረገው ጥምቀት እውነተኛ ጥምቀት አይደለም የሚሉ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከላይ እንደተገለጸው ሁሉ መሳሳታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሰውን ይመረጣል እንጂ ሰው እግዚአብሔርን አይመርጥም፡፡ ራሱ ባለቤቱ እንዳሰተማረው ሁሉ እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም ብሏል (ዮሐ. 15፡16)፡፡ ድኀነት በእግዚአብሔር ቸርነት የሚገኝ እንጂ በሰው ትምህርት እና እውቀት የሚሸመት ወይም የሚገበይ ዕቃ አይደለም፡፡
ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ሕፃናትን ማጥመቋ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደሙት አበው ባገኘችው ትምህርት መሠረት ነው፡፡